በግዕዝ ቋንቋ በሜዳሊያ የተመረቀው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳተኛ ተመራቂ።

12

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 6 ሺህ 492 ተማሪዎች አስመርቋል። በዕለቱ ከፍተኛ ነጥብ ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።

ከሜዳሊያ ተመራቂዎች መካከል የእይታ አካል ጉዳተኛው የማነብርሃን ወርቅዬ ይገኝበታል። ተሸላሚው የማነብርሃን በግዕዝ ቆንቋ 3 ነጥብ 32 በማስመዝገብ ነው በሜዳሊያ መመረቅ የቻለው።

በብዙ ወጣ ውረድ ለውጤት መብቃቱን የሚናገረው ተመራቂው አካል ጉዳተኝነት ከምንም እንደማያግድ አሳይቻለሁ ብሏል። በተለይ ብዙ የሀገራችን ታሪካዊ ቋንቋ በኾነው “ግዕዝ” በከፍተኛ ነጥብ በመመረቁ ደስተኛ መኾኑን ገልጿል።

“አካል ጉዳተኝችን ማስተማር ሀገርን ማስተማር ነው” የሚለው የሜዳሊያ ተሸላሚው አካል ጉዳተኞች ባለብሩህ አዕምሮ ስለኾኑ አስተምሮ ከችግር እንዲወጡ ማስቻል እና አዕምሯቸውን መጠቀም ይገባል ብሏል።

የግዕዝ ቋንቋ እንዲስፋፋ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ የተጀመረውን መማር ማስተማር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግሯል።

በቀጣይ የሥራ ዘመኑ የግዕዝ ቋንቋ መምህር በመኾን ማገልገል እንደሚፈልግ ገልጿል። የግዕዝ ቋንቋ እንዲያድግም የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል።

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

ፎቶ፦ በያየህ ፈንቴ

#አሚኮ-ዜና #ባሕርዳር-ዩኒቨርሲቲ #ምርቃት2018

Previous article‎”ሀገርን እና ወገንን በታማኝነት እና በሥነ ምግባር አገልግሉ” የሺእመቤት ደምሴ (ዶ.ር)
Next articleየጀጎል ዓለም ቅርስ የኮሪደር ልማት ሥራዎች “የወል ትርክት እሳቤዎች” ማሳያ ናቸው – ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ