‎”ሀገርን እና ወገንን በታማኝነት እና በሥነ ምግባር አገልግሉ” የሺእመቤት ደምሴ (ዶ.ር)

25


‎ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሠለጠናቸውን 2 ሺህ 45 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 618ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሳይህ ካሳው (ዶ.ር) የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች በችግሮች ውስጥም ኾነው በመውጫ ፈተና ላይ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

‎ይህ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስኬት እንጂ መጨረሻ አይደለም ብለዋል። በተመረቁበት የሙያ ዘርፍ ወገናቸውን እና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‎በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ.ር) ለተመራቂ ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ይህ ቀን ለተመራቂ ተማሪዎች የላቀ እውቀት እና የምርምር መጀመሪያ ምዕራፍ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሀገርን እና ወገንን በታማኝነት እና በሥነ ምግባር እንዲያገለግሉም አሳስበዋል፡፡

‎ከዓመታት ትጋት እና ልፋት በኋላ ለምረቃ በመብቃታቸው መደሰታቸውን ተመራቂ ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል፡፡ በተመረቁበት የሙያ ዘርፍ ሕዝባቸውን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

#አሚኮዜና #ደብረማርቆስዩኒቨርሲቲ #ተመራቂ2018

Previous articleየበጎፍቃድ አገልግሎት ችግር የሚፈታበት የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው።
Next articleበግዕዝ ቋንቋ በሜዳሊያ የተመረቀው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳተኛ ተመራቂ።