ተመራቂ ተማሪዎች ከዘመናዊው ዓለም ጋር ራሳቸውን ማዋሐድ አለባቸው።

18

 

ደባርቅ: ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መርሐ ግብሮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ባያብል ሙላቴ ተማሪዎች በቀጣይ የሕይዎት ምዕራፋቸው ጠንክረው በመሥራት ለሀገራቸው ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከዘመናዊው ዓለም ጋር ራሳቸውን ለማዋሐድ የሚያስችሉ ዕውቀት እና ልምዶችን ሊያዳብሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርጋቸው የዓለም ዓቀፍ ግንኙነቶች እና የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገዬ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን በጥናት እና ምርምር ተመስርቶ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከተቋማት ጋር ያለውን ልማታዊ አጋርነት በማጠናከር ለሁለንተናዊ የማኅበረሰብ ለውጥ እየሠራ ነው ብለዋል።

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ተማሪዎችን ለማብቃት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የአካዳሚክ፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ጋሻው ግስሙ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው የትምህርት መርሐ ግብሮችን በማስፋት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየሠራ ነው ብለዋል።

በጤና ሳይንስ ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ማስመረቁንም ጠቅሰዋል።

በመደበኛ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ የመውጫ ፈተና ውጤት በማምጣት ማለፋቸውንም ገልጸዋል።

የተመራቂ ወላጆች በበኩላቸው ተማሪዎችን በዕውቀት እና በልምድ በማብቃት በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ተመራቂ ተማሪዎችም በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት እና ልምድ በመጠቀም ውጤታማ ተግባር ለማከናዎን እንደሚተጉ ገልጸዋል።

“ትምህርት ሂደት ነው” ያሉት ተመራቂዎቹ በቀጣይም ለተሻለ የትምህርት እና የሥራ ዕድሎች ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

#አሚኮ-ዜና #ደባርቅ-ዩኒቨርሲቲ #ምርቃት2018

Previous articleከወሰዳቸው የትምህርት መስኮች 43ቱን A+ እና ዘጠኙን A በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የኾነው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ።
Next articleየበጎፍቃድ አገልግሎት ችግር የሚፈታበት የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው።