
ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 6 ሺህ 492 ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ ተመራቂ ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ከፍተኛ ትምህርት የሀገርን ገጽታ ለመቀየር እና ሕዝብን ከድህነት ለማውጣት አይነተኛ መሣሪያ መኾኑን ካደጉ ሀገራት ተሞክሮ እና ከታሪክ መረዳት ይቻላል ነው ያሉት።
ይህንን እውነታ ከግምት ውስጥ በማስገባትም በኢትዮጵያ ባለፉት ሦሥት አስርት ዓመታት የከፍተኛ ትምህርትን በማስፋፋት እና የክህሎት አቅምን በማሳደግ ረገድ መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የማሰብ እና የማገናዘብ ችሎታን የሚያዳብር፣ በራስ መተማመንን የሚያጎለብት፣ በአስተሳሰብ የበሰሉ እና ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት የላቀ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
እያንዳንዱ ተመራቂ ለሀገር ዕድገት እና ብልጽግና በየሙያው ጠንክሮ ሊሠራ እና “የሀገር አለኝታ” ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ተመራቂዎች ለቀጣዩ የሕይወት ዘመናቸው ለራሳቸው በሚያስቀምጡት የስኬት ትርጉም መሠረት ስኬታማ እና ደስተኛ መኾን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ተመራቂዎች ለቤተሰቦቻቸው አለኝታ በመኾን፣ ሀገራቸውን ካለችበት ድህነት ለማውጣት እና ሰላም የሰፈነባት ለማድረግ የበኩላቸውን የሚወጡ ብቁ ዜጎች መኾን እንደሚገባቸውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
#አሚኮ_ዜና #የባሕር_ዳር_ዩኒቨርሲቲ_ምረቃ #ባሕር_ዳር #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
