
አዲስ አበባ: ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም በአርባ ምንጭ ከተማ እየገመገመ ነው።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በበጀት ዓመቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች፦
👉 የማዘጋጃ ቤቶች ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል!
በ2014 በጀት ዓመት በማዘጋጃ ቤቶች ይገኝ የነበረው ገቢ 17 ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር። በ2018 በጀት ዓመት (መረጃው እስከተጠናከረበት ዕለት ድረስ) በከፍተኛ ዕድገት ከ111 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል ብለዋል።
በዚህም በርካታ ከተሞች ወጪያቸውን ከ30 እስከ 50 በመቶ መሸፈን ችለዋል። ውስን ከተሞች ደግሞ የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን መሸፈን ችለዋል ነው ያሉት።
🏗 የኮሪደር ልማት እና የወደፊት የከተሞች ፕላን፦
በበጀት ዓመቱ በኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ መቀየር ተችሏል። ከተሞች ቀደም ብለው በፕላን አለመደራጀታቸው ሥራውን አድካሚ ቢያደርገውም በትጋት ውጤት ተገኝቷል።
በቀጣይ ከተሞች ሥርዓት ያለው አደረጃጀት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከተማ ሊኾኑ የሚጠበቁ ከ5 ሺህ 100 በላይ ቀበሌዎች ፕላን እንዲኖራቸው ተደርጓል።
🏠 እየጨመረ የመጣውን የቤት ፍላጎት ማሟላት፦
የከተሞች የቤት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።
የመኖሪያ ቤት ማኅበራትን በማደራጀት፣ በመንግሥት እና በግል አጋርነት አማካኝነት የመኖሪያ ቤቶችን ለሕዝብ ለማቅረብ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ የክልል፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
#አሚኮ_ዜና #ከተማና-መሰረተ-ልማት-ሚኒስቴር #የኮሪደርልማት #Urbanization #Ethiopia #Infrastructure
