☕️ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ወደ 6 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ እየተሠራ ነው።

9

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ከቡና ወጭ ንግድ 3 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት መቃረቧን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ዛሬ የግብርና ሚኒስቴር እና የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በጋራ ባዘጋጁት “ሀገራዊ የቡና ልማት ፓኬጅ መተግበሪያ ሰነድ” የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በቡና ማምረት፣ መላክ እና ምርምር ላይ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዚህ መድረክ ላይ የኢትዮጵያን የቡና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ወሳኝ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

“ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀች ሀገር ብትኾንም እስካሁን ማግኘት የሚገባትን ተገቢ ጥቅም አላገኘችም” ነው ያሉት።

የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ:-

📌እንደ ብራዚል እና ቬትናም ያሉ ሀገራት በሄክታር 15 ኩንታል ሲያመርቱ የኢትዮጵያ ግን አኹንም 8 ኩንታል ማምረት ላይ ናት። ዛሬ ለውይይት የቀረበው ሰነድ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ምርታማነታችንን በሄክታር ወደ 21 ኩንታል ለማድረስ ያለመ ነውም ብለዋል።

📌ከባሕላዊ አሠራር ወጥቶ በአየር ንብረት ለውጥ እና በሽታን የሚቋቋሙ፣ ምርታማነትን የሚጨምሩ አዳዲስ ዝርያዎችን በምርምር ማምጣት ይገባል ነው ያሉት።

📌50 በመቶ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና 50 በመቶ የኬሚካል ማዳበሪያን በመጠቀም ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

📌ከዝናብ ጥገኝነት ወጥቶ በመስኖ ማምረት፣ ከትንንሽ የገበሬ ማሳዎች ወደ ሰፋፊ እና ኮሜርሻል እርሻዎች መሸጋገር ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።

📌በአንድ ሄክታር የነበረውን ከ1ሺህ 600 እስከ 2ሺህ 500 የቡና ችግኝ ቁጥር ከፍ ለማድረግ የጋራ ርብርብ ያስፈልጋልም ብለዋል።

እነዚህን ዘመናዊ አሠራሮች በአግባቡ በመተግበር ጥራቱን የጠበቀ የቡና ደረጃ በማምረት አኹን ያለውን የ3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ግኝት ወደ 6 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ተብሏል።

ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ

#አሚኮ_ዜና #Ethiopia #Ethiopian_Coffee #Agriculture #Economy #Export #MoA #ECTA #Coffee_Development

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች አስመረቀ።
Next articleየከተሞች የማዘጋጃቤታዊ ገቢ እያደገ መምጣቱን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።