
ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 6 ሺህ 492 ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ለተመራቂዎች፣ ለተመራቂ ወላጆች እና ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ተመራቂዎች ከዛሬ ጀምሮ ስማችሁ የሚጻፈው የዩኒቨርሲቲው አካል እና ተመራቂ ብቻ ኾናችሁ ሳይኾን በኢትዮጵያ የወደፊት የለውጥ አካል ተደርጋችሁ ነው ብለዋል። ብዙ ውጣ ውረድን አልፎ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም መመረቅ ቀላል አይደለም ያሉ ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ሁሉንም ተቋቁመው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱበት እና የተሸጋገሩበት መኾኑን ገልጸዋል።
ከእያንዳንዱ ተመራቂ ጀርባ የሚደግፍ እና የሚያበረታታ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሀገር፣ መምህራን፣ ተመራማሪ፣ ባለሙያ እና ሌላም አለ ነው ያሉት።
አንጋፋው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ግዙፍ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንደኛው እንደኾነ ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ መኾኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በእውቀት፣ በምርምር እና በሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት። ወደ ሰማይ ስናይ የኤሮስፔስ ወደ መሬትና ባሕር ስናይ በማሪታይም ዘርፍም ተማሪዎችን በማስተማር ለሀገር እድገት እና ደኅንነት እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
“ዩኒቨርሲቲው በሚያስመርቃቸው ተማሪዎች ብቻ አይለካም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይልቁንም በሚፈታው ችግር ነው” ብለዋል። ለዚህም የተለያዩ ችግር ፈቺ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ ገዝነት ሲሸጋገር ያለው ራዕይ ልህቀት እና ኀላፊነትን አብሮ የሚያይበት፤ ፈጠራ ከኅብረተሰብ ፍላጎት ጋር የሚጣጥምበት፤ ዕውቀት መፍትሔ የሚኾንበትን ተቋም ገንብቶ ማየት እንደኾነም ገልጸዋል።
ተመራቂዎች ዛሬ የትምህርታችሁ መጀመሪያ እንጅ መጨረሻ አይደለም ብለዋል። ሁሌም ማንበብ ራስን ማሳደግ እና ለሀገር መፍትሔ ኾኖ መገኘት በቀጣይም ከተመራቂዎች እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል። ተመራቂዎች የዕውቀት አገልጋዮች ናችሁ ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
#አሚኮ-ዜና #ባሕርዳር-ዩኒቨርሲቲ #ምርቃት2018
