
ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በጽሕፈት ቤታቸው ችግኝ ተክለዋል።
በችግኝ ተከላው ከርእሰ መሥተዳድሩ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ተሳትፈዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከቢሮ እስከ ሀገር የተዘረጋ ትልቅ ንቅናቄ ነው። ኢትዮጵያን አረንጓዴ ካባ የማልበስ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ እንዳትበገር የማድረግ፣ ምርት እና ምርታማነትን መጨመር እና የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ግብ ይዞ እየተተገበረ የሚገኝ ንቅናቄ ነው።
ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ በኢትዮጵያ 48 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል። በአማራ ክልል ደግሞ ከ10 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በችግኝ ተሸፍኗል።
በአማራ ክልል በ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች ይተከላሉ ተብሏል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ሰኔ 18/2018 ዓ.ም በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ እንጉቲ ቀበሌ ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ባስጀመሩበት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደ ክልልም ኾነ እንደ ሀገር ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን አንስተዋል። የአርሶ አደሮችም ሕይወት እየቀየረ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘንድሮ ለአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠ አንስተዋል። የአትክልት እና ፍራፍሬን ከተቆራረጠ ልማት ወደ ኩታገጠም ማሸጋገር እንደሚገባም መናገራቸው ይታወሳል።
አረንጓዴ አሻራ የቤተሰብ ገቢን ያሳደረጋል፣ የምግብ ዋስትናን ያረጋግጣል፣ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል ነው ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የነገ ተስፋ የሚተከልበት ነው፤ ዛሬ የተክልነው ለነገ ተስፋዎቻችን ይኾናሉ፣ ለነገ ተስፋዎች የሚኾኑንን ዛሬ ላይ እንትከል ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በገጠር እና በከተማ መተግበር እንዳለበትም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ እና ምቹ የአየር ንብረት ለመፍጠር ከቢሮ እስከ ሀገር ድረስ ችግኞችን መትከል፣ የተተከሉትን ተንከባክቦ ማጽደቅ እና ለጥቅም ማዋል ይገባል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
#አሚኮ #አሚኮዜና #አማራክልል #ርእሰመሥተዳድር #ኢትዮጵያ #ኤንጓዴአሻራ
