🇪🇹 የትላንት አደራን ለመወጣት የሚታትሩ ኢትዮጵያውያን ለነገም ታሪክ እየተከሉ ነው።

9

 

ኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ማኅደር እና የበርካታ ድንቅ ቅርሶች ባለቤት ናት። እነዚህ ቅርሶች የማንነቷ ሕያው መስታወቶች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ ዞኑ የሚታወቅበትን የባሕል ጭፈራ በታደሙበት ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን “የኢትዮጵያ አንድነት ገመድ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ቅርሶች የጥንታዊ ኢትዮጵያውያ ደማቅ ታሪክ ህያው ምስክሮች መኾናቸውንም ተናግረዋል። ቅርሶቹን ለዛሬው ትውልድ ያሻገረው ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተሰማርቶ ታሪክ ሢሠራ መኖሩን በግልጽ ያሳያሉ ነው ያሉት።

ቅርሶችን ጠብቆ እና አድሶ ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር የዘመኑ ታላቅ አርበኝነት የነገ መታወሻም ነው ይላሉ።

ከዚህም ባለፈ ቅርሶችን የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ መጠበቅ እና አሻራቸውን ማስቀጠል ይገባል። ለዚህም በቅርቡ የተከናወኑ የቅርስ እድሳት ሥራዎች ትልቅ ማሳያ ናቸው።

የብሔራዊ ቤተ መንግሥት የቀደመ ክብሩ ከነነባር ውበቱ ጋር ተመልሷል። በአሁኑ ወቅትም ለሕዝብ እና ለውጭ ጎብኝዎች ክፍት ኾኗል። የመፍረስ አደጋ ተደቅኖበት የነበረው የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥንታዊ ይዘቱን ጠብቆም ታድሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ላይም እንዳብራሩት ቅርሱ አልታደሰም፤ ዳግም ተወለደ እንጂ በማለት ቅርሶች ነባር ይዞታቸውን ሳይለቁ በማደስ ዕድሜያቸውን ማርዘም እንደሚቻል ተናግረዋል።

በከተማ መስፋፋት ጫና ስር ወድቆ የነበረው የሐረር ጀጎል ግንብ የውስጥ እና የውጭ ገጽታው ታድሶ ለከተማዋ አዲስ ገጽታን አጎናጽፏታል።

የጅማው አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ ተፈጥሯዊ ውበታቸውን ሳይለቁ ዕድሳት ተደርጎላቸዋል።

የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ ማስመስከሪያ የኾኑት እነዚህ እና ሌሎች ቅርሶች ዕድሳታቸው በፍጥነት ተጠናቅቆ ዕድሜያቸው የረዘመው፣ በጉብኝት ኢኮኖሚ ወደ ማመንጨት የገቡት በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እና ቁርጠኝነት ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በፌዴራል እና በክልል ከፍተኛ መሪዎች የተሰጠው የባለቤትነት ትኩረት በአጭር ጊዜ ጀምሮ የማጠናቀቅ ውጤት መሰረቶችም ናቸው።

ማኅበረሰቡም ቅርሱን እንደ ማንነቱ አጥብቆ ይዟል። የአካባቢው ነዋሪ ቅርሶችን ከሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች በንቃት እየጠበቀ ነው። ለእድሳት ሥራዎችም የጉልበት እና የሞራል ድጋፍ በማድረግ የማይተካ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።

ቅርሶች የትላንት አደራዎች ብቻ ሳይኾኑ የነገ ብሩህ ትሩፋቶችም ጭምር ናቸው።

#አሚኮ_ዜና #ቅርስ_ለኢኮኖሚ_ልማት #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ

Previous articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት 6 ሺህ 492 ተማሪዎችን ያስመርቃል።
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በጽሕፈት ቤታቸው ችግኝ ተከሉ።