ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።

10

 

አደሴ: ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለ18ኛ ዙር በመደበኛ እና በርቀት ትምህርት ያሠለጠናቸውን 843 ተማሪዎችን አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በልዩ ልዩ የትምህርት ክፍሎች ከፍተኛ ውጤት እና የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የዋንጫ እና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ.ር) አሁን ላይ ያለው የቴክኖሎጂ ዘመን ተመራቂዎች ከመንግሥት ወይም ከሌሎች አካላት ሥራ የሚጠብቁ ሳይኾን የራሳቸውን የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲኾኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከዕውቀት ባሻገር በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ የምትሻበት ወቅት በመኾኑ ተመራቂ ተማሪዎች በተሰማሩበት መስክ ሁሉ በቅንነት፣ በታማኝነት እና በሀቀኝነት ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው ተመራቂዎች በቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት በተግባር በመለወጥ እና የሚያጋጥሟቸውን ልዩ ልዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ወደ መልካም ዕድሎች በመቀየር ግንባር ቀደም መኾን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በከፍተኛ ውጤት ተመርቀው ሽልማት የተበረከተላቸው ተማሪዎች ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ጥራት ያለው ዕውቀት ከመቅሰም ባለፈ መልካም ስብዕናን እና ሙያዊ ሥነ ምግባርን እንዲላበሱ ትልቅ እገዛ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።

ለትምህርታቸው በሰጡት ከፍተኛ ትኩረት እና ትጋት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውንም ጠቁመዋል። ተመራቂዎቹ በቀጣዩ የሥራ ዘመናቸው እና በሰፊው ዓለም ውስጥ ዕውቀታቸውን ተጠቅመው ሀገራቸውን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን አመላክተዋል።

#አሚኮ_ዜና #የወሎ_ዩኒቨርሲቲ_የተማሪዎች_ምረቃ #አማራ_ክልል

ዘጋቢ፦ሰልሀዲን ሰይድ

Previous articleየፕሪቶሪያን ስምምነት የጣሰው ሕወሓት ዛሬም ከአሮጌው መንገድ አልተላቀቀም
Next articleየብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ የውይይት መድረክ በጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀመረ።