
በ2013 ዓ.ም ሕወሓት የፌዴራል መንግሥትን በኀይል ሥልጣን ለመረከብ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።
በወቅቱ በማይካድራ፣ በጭና እና በበርካታ ቦታዎች ንጹሐንን በመጨፍጨፍ በርካታ ንብረቶችን በማውደም በዜጎች ላይ ጉዳት አድርሷል።
በመጨረሻም መንግሥት በወሰደው መጠነ ሰፊ እርምጃ ተሸንፎ የነበረው የሕውሓት ቡድን የፕሪቶሪያን ውል ተፈራርሟል። በወቅቱ ኢትዮጵያ ያሸነፈች ቢኾንም መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ለሕዝብ እፎይታ እና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የፕሪቶሪያን ውል ፈርሟል።
የፕሪቶሪያው ውል ይፈጸም ዘንድ መንግሥት በፍጥነት ወደ ተግባር በመግባት ለትግራይ ክልል ከፍተኛ በጀት በመመደብ፣ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት በማስጀመር፣ የምግብ እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ፣ በጦርነት የወደሙ የመሠረተ ልማቶችን በመገንባት እና በሌሎች ተግባራት የፕሪቶሪያን የውል ስምምነት ለመፈጸም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
ኾኖም ጦርነት እና ግጭት የልብ ትርታው የኾነው የሕወሓት ቡድን የፕሪቶሪያን ስምምነት በማፍረስ አሁንም ወደቀደመ የግጭት አባዜው እየገባ ይገኛል።
ሕወሓት ትጥቅ ሙሉ በሙሉ ባለመፍታት፣ ተዋጊዎቹን ወደ ተሀድሶ ባለመመለስ፣ ተፈናቃዮችም እንዳይመለሱ በግድ በመያዝ የእርዳታ መለመኛ እና እርዳታውንም ለጥይት መግዣ በማድረግ የፕሪቶሪያውን ውል ሳይፈጽም ቀርቷል።
ከፕሪቶሪያ ስምምነት እና ከሀገር ሕገ መንግሥት ባፈነገጠ መልኩ ከውጭ አካላት ጋር የሴራ ግንኙነት እያደረገም ነው። መንግሥት ለሰላም ካለው ፍላጎት አንጻር ታግሶት ቢቆይም አሁን ደግሞ በግልጽ ወደ ሌላ ግጭት ለመግባት ትንኮሳ እያደረገ ነው።
በቅርቡ በመገናኛ ብዙሀን ይፋ የተደረገ የጥናት ውጤት እንደሚያመላክተው ሕውሓት ወጣቶችን በማስገደድ እና በማፈን ለጦርነት እንዲዘጋጁ እያደረገ ስለመሆኑ ያብራራል።
የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት እኩይ ሴራ በመራቅ እና በመታገል ሰላሙን ሊጠብቅ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያየ ጊዜ ከሚዲያዎች ጋር በነበሯቸው ቆይታ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በየካቲት ወር 2018 ዓ.ም በትግረኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት ሕወሓት በአሮጌው መንገድ ለመጓዝ መሞከሩ ለግጭት ዳርጎታል ብለዋል።
የትግራይ ወጣቶች በአሮጌ አስተሳሰብ ለጦርነት ከሚገፋፏቸው አካላት ራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። መንግሥት በትግራይ ክልል ሰላም እንዲሰፍን እና ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ጽኑ ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል።
ከሰሞኑ የሕወሓትን የግጭት ቀስቃሽነት እና የሰላም ጸርነትን የተረዳው የአሜሪካ መንግሥትም በሕወሓት መሪዎች እና ቤተሰቦች ላይ የቪዛ እገዳ በማድረግ ለዓለም ሕዝብ ኢትዮጵያውያን በዕውነት ላይ ተመሥርተው የሕወሓትን ቡድን እንደሚያወግዙ አረጋግጧል።
ግጭቱ መጀመሪያ የሚጎዳው የትግራይን ሕዝብ ሲቀጥልም የሀገር ኢኮኖሚን በመኾኑ ቆም ብሎ ማሰብ ከትግራይ ሕዝብ ይጠበቃል። በተለይም የትግራይ ሕዝብ ለጦርነት ተባባሪ ባለመኾን በሰላም መኖርን መምረጥ ይኖርበታል።
#አሚኮ_ዜና #ሰላም #ኢትዮጵያ 🇪🇹
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
