ነዳጅን በሕገ ወጥ መልኩ በተጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል።

4

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ በወቅታዊው የነዳጅ እጥረት ሳቢያ የተፈጠሩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ባለፉት ወራት ያከናወናቸውን የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ገምግሟል።

የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ከዓለም አቀፍ የነዳጅ እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ በክልሉ የትራንስፖርት እና የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አጋጥሞ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ችግሩ የትራንስፖርት ስምሪት መዛባት እንዳያስከትል ለሕገ ወጦችም ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጥር ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጣ ግብረ ኃይል በማቋቋም በየደረጃው ጠንካራ የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ለሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ በተደረገ የተቀናጀ ቁጥጥር ከ490 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች (በድግግሞሽ) ላይ ፍተሻ መደረጉንም ተናግረዋል። ከእነዚህም ውስጥ ከ54 ሺህ በላይ የሚኾኑት ጥፋተኛ ኾነው ተገኝተዋል ነው ያሉት። በእነዚህ ጥፋተኞች ላይ በተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ከ74 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

ባለፉት 50 ቀናት በተከናወነ ጥብቅ የቁጥጥር ሥራ ከ190 በላይ በሚኾኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ተገጥመው የነበሩ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ማስተላለፊያዎች (ሳልቫቲዮ) እንዲወርዱ እና እንዲስተካከሉ ተደርጓል ነው ያሉት።

627 ተሽከርካሪዎች ነዳጅን ላላስፈላጊ አላማ በማዋል የነዳጅ አቅርቦትን አደጋ ላይ ጥለው በመገኘታቸው ከትራፊክ እና ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቁመዋል።

ከተገቢው ታሪፍ በላይ በማስከፈል ሕዝቡን ሲያጉላሉ በነበሩ አካላት እና በወቅቱ የቴክኒክ ምርመራ ሳያደርጉ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ጥፋተኞችን በማስተማር እና በመቅጣት የተሠራው ሥራ በመንገድ ደኅንነት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።

በቀጣይም የቁጥጥር ሥራው በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲኾን፣ የበታች መዋቅሮች በቁርጠኝነት ወደ ሥራ እንዲገቡ እና ተሞክሮዎችን ማስፋት ወሳኝ መኾኑ ተመላክቷል።

ደንቦችን እና ልዩ የስምሪት መቆጣጠሪያ መመሪያዎችን በማሻሻል በመንገድ ደኅንነት ላይ የሚያጋጥሙ ተደጋጋሚ ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል በነዳጅ እጥረት፣ ስርቆት እና ሕገ-ወጥ ዝውውር ምክንያት በዋና ዋና ከተሞች ተፈጥሮ የነበረውን ከፍተኛ ቀውስ እና የስጋት ድባብ ማክሸፍ መቻሉንም ተናግረዋል።

ይህ በግብረ ኃይሉ የተሠራው የተቀናጀ የቁጥጥር፣ የሕግ ማስከበር እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ የተሳካ የማረጋጋት ውጤት ማምጣቱንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርሙን ለማሳካት በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው።
Next articleየፕሪቶሪያን ስምምነት የጣሰው ሕወሓት ዛሬም ከአሮጌው መንገድ አልተላቀቀም