
ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በመጀመሪያው ዙር ወደ መንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም የሚገቡ ተቋማትን የቅድመ ዝግጅት ሁኔታ በተመለከተ በባሕር ዳር ከተማ እየተገመገመ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም በአማራ ክልልም ወደ ተግባር እየገባ ነው ብለዋል።
በእስካሁኑ ሂደት የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ የማጥራት እና የመመዝገብ ሂደት በዞኖች፣ በከተማ አሥተዳደሮች እና በወረዳዎች እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በክልል ደረጃም ስምንት ተቋማትን በመለየት ወደ ሪፎርም ሥራዎች ገብተዋል ነው ያሉት።
የተጀመረው የሪፎርም ሥራ ቅንጅትን የሚጠይቅ፣ ጠንካራ የአመራር ቁርጠኝነትን የሚፈልግ እና የቴክኖሎጂ እገዛን የሚጠይቅ ነው ብለዋል። ሪፎርሙን ለማሳካትም በተሻለ ቁርጠኝነት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንቺአምላክ ገብረ ማርያም መድረኩ የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርምን ወደ ተግባር ለማስገባት በስምንት ተቋማት የተጀመረውን የዝግጅት ምዕራፍ ለመገምገም ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
እንደ ክልል ስምንቱም ተቋማት ለሪፎርሙ አተገባበር በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጁ መኾናቸውን ነው የገለጹት። ሪፎርሙ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ተግባር በማስገባት እና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን በመሥራት በውጤታማነት እየተተገበረ መኾኑን አንስተዋል።
በሪፎርሙ አተገባበር ባለሙያዎች እና በመሪዎች ግንዛቤ ይዘው እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል። በመጀመሪያው ዙር ወደ ትግበራ የሚገቡት ስምንት ተቋማትን ተሞክሮ በማጠናከር በቀጣይ ሐምሌ ወር ጀምሮ ደግሞ ዘጠኝ ተቋማት እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
