
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ረጅም ታሪክ፣ ጠንካራ ሕዝብ እና ትልቅ የውጭ ግንኙነት ልምድ ያላት፤ የነፃነት ተምሣሌት የኾነች፤ በታሪኳም ኾነ በአሁኑ ወቅት ለውይይት፣ ለዲፕሎማሲ እና ለአብሮ ማደግ ቅድሚያ የምትሰጥ፤ ሰላም ወዳድ የኾነች፤ በጂኦፖለቲካዊ ስትራቴጂክ ሥፍራ ላይ የምትገኝ፤ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲጠናከር የበኩሏን ሚና እየተወጣች የምትገኝ ሀገር ናት ኢትዮጵያ።
በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶቿ ወደኋላ ሊጎትቷት ቢሞክሩም ለጎረቤቶቿ ሰላም የምትመኝ፣ ለበደሏት ይቅርታ የምታደርግ እና ወደፊት በዕድገት መገስገስን ዓላማ ያደረገች የቀጣናው ኀያል ሀገር መኾኗን በተግባር አረጋግጣለች።
የአሁኗ ኢትዮጵያ መገለጫዎች፦
🇪🇹 ትንኮሳዎችን በትዕግስት በማለፍ ለራሷ ዕድገት እና ለሰላም ቅድሚያ ትሰጣለች።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከጎረቤት ሀገራት እና ከውስጥ ታጣቂዎች ከፍተኛ ትንኮሳዎች እና ጫናዎች ደርሰውባታል። እየደረሱባትም ይገኛል። ከግብጽ፣ ከሱዳን እና ከኤርትራ በኩል የሚመጡ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ትንኮሳዎችን ብስለት በተሞላበት ጠንካራ ዲፕሎማሲ ማለፍ ችላለች።
በሀገር ውስጥ ከውጭ ጠላቶች ተልዕኮ የተቀበሉ የሕወሓት ቡድን እና ሌሎች ታጣቂዎች የሀገሪቱን ሰላም ለማናጋት የከፈቱትን ትንኮሳ በበላይነት በመቀልበስ፣ ትኩረቷን ወደ ጦርነት ሳይኾን ወደ ልማት አዙራ መቆየቷም የሚታወስ ነው።
🇪🇹 በፈተና ውስጥ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በስኬት መገንባትም ችላለች።
ሀገሪቱ የውስጥ ሰላሟን ለማስከበር የምታደርገው ጥረት የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከማሳለጥ አላገዳትም። ይልቁንም ከምንጊዜውም በላይ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች።
የውስጥ እና የውጭ ጫናዎችን በጽናት በመቋቋም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን በማጠናቀቅ የውኃ ሙሌት እና የኀይል ማመንጨት ሥራዎችን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቃለች።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሠሩት የኮሪደር ልማቶች የሀገሪቱን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይረዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ኮስማና ስም ወደ በለጸገች ሀገርም ቀይሯል። በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ የተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ እንዲሁም በበጋ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ውጤታማነት ፍንትው አድርገው አሳይተዋል።
🇪🇹 በአለት ላይ የተገነባው የይቅርታ፣ የእርቅ እና የሆደ ሰፊነት ተምሳሌትነቷ አሁንም በብርቱ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ የቱንም ያህል በውስጥ ግጭቶች ብትፈተንም ነገን ለማዳን ዛሬ ይቅር ማለትን የመረጠች ሀገር ናት። ከታጠቁ ኀይሎች ጋር የተደረጉ የሰላም ስምምነቶች ሀገሪቱ ለሕዝቧ ደኅንነት ስትል የምትከፍለውን መስዋዕትነት የሚያሳዩ ናቸው። የተቋቋመው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ለዘመናት የቆዩ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ያላትን ብርቱ አቋም ያሳየ ነው። ታዲያ ይህ የጥላቻን ግንብ የማፍረስ የቀደሙትን በደሎች የመተው እና ኹሉንም ዜጎች አቅፎ ለመጓዝ የምታደርገው ጥረት ለሌሎች ሀገራት ጭምር ትልቅ ትምህርት የሰጠ ኾኗል።
🇪🇹 ኢትዮጵያ ከራሷ ዜጎች አልፎ ለሰው ልጆች ሰላም መስዋእትነት የምትከፍል ሀገር ናት። ኢትዮጵያ የራሷ ሰላም አስተማማኝ እንዲኾን አበክራ ትሠራለች። “የጎረቤትህ ሰላም የአንተም ሰላም ነው” በሚል እሳቤም የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የተረጋጋ እንዲኾን ቀዳሚውን ሚና እየተወጣች ትገኛለች። በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በአብዬ ክልል የተሰማሩ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ለቀጣናው መረጋጋት የገበሩት ውድ ሕይወት ለዚህ ሕያው ምስክር ነው። በቀጣናው ባሉ የጎረቤት ሀገራት በጦርነት ምክንያት የሚሰደዱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መጠለያ፣ ማረፊያ እና መጠጊያ ኾናም ቆይታለች።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ በትዕግስት እና በጥበብ ፈተናዎችን የምታልፍ፣ በይቅርታ ጽኑ መሠረት የምትገነባ እና በልማት የምትገሰግስ ሀገር ናት። ይህንን ጉዞ ይበልጥ ለማሳደግ ታዲያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አወንታዊ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ እሙን ነው።
#አሚኮ_ዜና #ልማት_ዕድገት #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
