🥑 በአማራ ክልል ለአቮካዶ ምርት ትኩረት ተሰጥቶታል።

7

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአቮካዶ ምርት በአማራ ክልል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠው የመጣ እና በፍጥነት እያደገ ነው። በተለይም የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በማምረት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል።

እንደ አማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ ምርቱን ለማምረት የሚኾን ምቹ መሬት እና የአየር ንብረት ጸጋ በክልሉ አለ፡፡ በክልሉ ወደ 85 የሚጠጉ ወረዳዎች አቮካዶን በስፋት ያመርታሉ። ጸጋው ካለባቸው አካባቢዎች መካከል ሰሜን ጎጃም ዞን አንዱ ነው።

በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ የቆጋ አካባቢ ነዋሪ አርሶ አደር ሻረው በላይ ቀደም ሲል የአቮካዶ ምርት በብዛት በአካባቢው ይመረት እንደነበር ነግረውናል።

አቮካዶ አምራች አርሶ አደሮች ማኅበር መሥርተው የሚያመርቱትን ምርት ለውጭ ገብያ የሚያቀርቡበት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበርም አስታውሰዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ምርቱን ለውጭ ገብያ ማቅረብ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን በግብርና ጽሕፈት ቤት እገዛ ቆጋ አካባቢ የአቮካዶ ተክል ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል። አሁን ላይም ተከላ መጀመሩን ነው የተናገሩት።

የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ እንደ ዞን በዚህ ዓመት ከሚተከሉ 1 ሚሊዮን የአትክልት እና ፍራፍሬ ተክሎች መካከል ቡና እና አቮካዶን በተለየ ኹኔታ በመትከል የዞኑ መታወቂያ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነ ተናግረዋል። በዚህም ከ100 ሄክታር በላይ መሬት በአቮካዶ እና ከ100 ሄክታር በላይ መሬት ቡናን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በአትክልት እና ፍራፍሬ ዘርፍ የኩታገጠም አሠራር በዞኑ ተጀምሮ ቆይቷል ያሉት ኀላፊው ሰሜን ሜጫ ወረዳ በኩታገጠም አቮካዶ የሚተከልበት አካባቢ እንደኾነም ጠቅሰዋል።

ይህም ወደ ሌላው አካባቢ ያልሰፋበት እና ሰሜን ሜጫ ላይም ተቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ግን የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ ለማስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ስር የሚንቀሳቀሰው የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮግራም ሥራ አሥኪያጅ ይበልጣል ወንድምነው በሀገር አቀፍ ደረጃ የአቮካዶ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ተግባራዊ እየተደረገ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ በአማራ ክልል 39 ወረዳዎችን እንደሚደግፍም ገልጸዋል፡፡ በተያዘው ዓመትም በአማራ ክልል ስድስት ወረዳዎች ላይ የተሟላ ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን ነው የጠቀሱት፡፡‎ በዚህም በእነዚህ የተመረጡ አካባቢዎች በትላልቅ ኩታገጠም 950 ሄክታር መሬት የሚሸፍን አቮካዶ ለማልማት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡

‎ፕሮግራሙ ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን ተደራሽ ማድረግ ነው ያሉት ሥራ አሥኪያጁ አርሶ አደሮች በሰፋፊ ኩታገጠም አቮካዶ በማምረት ምርቱን በተሻለ ዋጋ ያለምንም እንግልት ለገበያ እንዲያቀርቡ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሚያግዙ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበአማራ ክልል ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የበጎ አድራጎት ሥራ ለማከናወን ወደ ተግባር ተገብቷል።
Next articleስለ ሰላም አብዝታ ትታገሳለች፤ ለይቅርታም በሯን ትከፍታለች!