
ተሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል የክረምት በጎ አድራጎት ሥራዎችን “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ክንዋኔዎች አስጀምረዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገራችን ከጥንት ጀምሮ የነበረ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለሰው ተኮር ሥራዎች በተሰጠው ትኩረት ደግሞ የበለጠ የጎለበተ እሴት ነው ብለዋል።
በ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ አድራጎት ሥራ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማትን በማቀናጀት የዛሬውን ትውልድ የሚጠቅሙ ብቻ ሳይኾን ለነገው ትውልድም የሚሻገሩ በጎ ተግባራትን እናከናውናለን ነው ያሉት።
በ2018 ዓ.ም በአማራ ክልል የሚከናወነው የክረምት በጎ አድራጎት ሥራ በ17 ዋና ዋና የስምሪት መስኮች ከ50 በላይ በሚኾኑ ተግባራት በአግባቡ ተደራጅቶ እየተመራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል። 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሕዝብ በአገልግሎቱ ይሳተፋል፤ ከ15 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ይኾናሉ፤ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት መንግሥት እና ሕዝብ ሊያወጣው የሚችለውን ሃብትም ለማዳን ይሠራል ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የክረምት በጎ አድራጎት ሥራ ትላልቅ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሥራዎች እየተከናወኑበት ያለ እሴት ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ውስጥም አቅመ ደካማዎችን በመርዳት፣ አዳዲስ ቤቶችን በመሥራት እና አሮጌውን በመጠገን የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በተያዘው የክረምት በጎ አድራጎት ሥራ በከተማዋ 230 አዳዲስ ቤቶችን በመገንባት ለአቅመ ደካማዎች ለማበርከት እና በርካታ አሮጌ ቤቶችንም ለመጠገን መታቀዱን ገልጸዋል።
በጎነትን በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በመፈጸም የባሕር ዳር ከተማን ውበት የሚጨምሩ ችግኞችን የመትከል ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
#አሚኮ #አሚኮዜና #አማራክልል #በጎ-አድራጎት #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
