
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል የክረምት በጎ አድራጎት ሥራዎችን “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ክንዋኔዎች አስጀምረዋል።
በበጎ አድራጎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ከተከናወኑ የበጎነት ተግባራት መካከል ችግኝ ተከላ፣ ደም ልገሳ፣ ማዕድ ማጋራት፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ማሠራት፣ የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ እና በከተማዋ እየተሠራ የሚገኘውን የ100 እናቶች የገቢ ማስገኛ የገቢያ ማዕከል ግንባታ ጉብኝት ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የበጎ አድራጎት ሥራ በመላው የክልሉ አካባቢዎች በከተማም ኾነ በገጠር ሁሉም ሰው ገቢራዊ ማድረግ ያለበት እሴት ነው ብለዋል።
የበጎ አድራጎት ሥራ በተለያዩ ተግባራት እንደሚገለጥ ጠቅሰዋል። በተለይም የተራቆቱ መሬቶችን አረንጓዴ በማልበስ የሰዎችን እና የምድርን ጤናማ መሥተጋብር ለመጠበቅ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መሳተፍ እንደሚገባ አመላክተዋል።
“ትናንት ለምድራችን ጤና የሚበጀውን አረንጓዴ አሻራ፣ ዛሬ ደግሞ የመረዳዳት እና የአብሮነታችን ከፍታ የኾነውን የክረምት በጎ አድራጎት አስጀምረናል” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሁለቱንም ሥራዎች አስተሳስሮ በማከናወን ውጤት ማምጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ማኅበራዊ መረዳዳት የኢትዮጵያውያን የቆየ ባሕል ነው፤ ግለኝነትን በመቀነስ ይህንን ባሕል ከፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ሰው መኾንን እናስቀድም፤ ረዳት የሌላቸውን ቀድመን በመድረስ እንደግፍ፤ ቤታቸው የዘመመባቸውን በትብብር እናቃና ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ በመልዕክታቸው። በተያዘው ክረምት 9 ሺህ 634 አዳዲስ ቤቶች ተሠርተው ለአቅመ ደካሞች ይተላለፋሉ። ከ18 ሺህ በላይ ቤቶችንም በበጎ አድራጎት ለመጠገን መታቀዱን አንስተዋል።
በጋራ መቆም ከባድ የሚመስሉ ሥራዎችን በቀላሉ ለመሥራት እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል። በመላ ክልሉ የሚገኙ መሪዎች፣ በጎ አድራጊዎች እና መላው ሕዝብ በጎ ተግባራትን በማከናወን ደካሞችን በማቃናት እና የጎደለውን በመሙላት ተሳታፊ እንዲኾኑም ጥሪ አቅርበዋል።
የሕዝብን ደግነት ማንም ሊተካ አይችልም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በተለይም ሕዝቡ በበጎነት እሴቶች ላይ በንቃት መሳተፍ እና መደጋገፍ እንዳለበት ገልጸዋል። ከሕዝቡ ውስጥ ደግሞ በተለይም የሃይማኖት አባቶች በልዩ ኀላፊነት በጎነትን ለተከታዮቻቸው ማስተማር እና መምራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
#አሚኮ #አሚኮዜና #በጎአድራጎት #ባሕርዳር #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
