
ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 57ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማኅበር ጋር በተፈረሙ ሦሥት የፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሚውል የአራት መቶ ሰላሳ ሰባት ሚሊዮን አራት መቶ ሺ (437,400,000) ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡ ሁለተኛው የማኅበረሰብ ተኮር የመሬት አያያዝ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል የአንድ መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ (145,500,000) ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡ ሦሥተኛው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመስኖ ልማት ለዘላቂ ምርታማነት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሀምሳ አራት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺ (54,600,000) ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡ ምክር ቤቱም ሦሥቱ የብድር ስምምነቶች ከሀገራችን የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መኾናቸውን በማረጋገጥ የብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ተቋማት ለሚሰጧቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቷል፡፡ ተቋማቱ ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች በውስጥ ገቢ የሚሸፈኑ ወጪዎችን ከአገልግሎት ተጠቃሚዎች በሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ ለመሸፈን እንዲችሉ የአገልግሎት ተጠቃሚውን አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት በጥራት መስጠት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንዲያስችሉ ረቂቅ ደንቦቹ ተዘጋጅተው ለምክር ቤቱ ቀርበዋል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. ከዚያም ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው ለኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ማቋቋሚያ ስምምነት የአባልነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክን በአባልነት መቀላቀሏ ለሀገራዊ የልማት ፋይናንስ፣ ለመሠረተ ልማት ድጋፍ እና ለማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ለማግኘት የሚያስችላትና ከደቡብ ደቡብ የፋይናንስ ሥርዓቶች ጋር የሚኖራትን ትስስር የሚያጠናክር መኾኑ ስለታመነበት የባንኩን የመመስረቻ ስምምነት ለማጽደቅ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሀገራችን ዕድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት እንደመኾኑ በ2006 ዓ.ም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ወጥቶ ላለፉት ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል፡፡ በዚህም በኢንዱስትሪው አንዳንድ ለውጦች የተመዘገቡ ቢኾንም ዓለማችን ከደረሰችበት የቴክኖሎጂ እድገት፣ የከተሞች መስፋፋት፣ የመሰረተ ልማቶች ፍላጎት ማደግ አንጻር ሰፊ ክፍተት የነበረበት በመኾኑ የዘርፉን ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ፣ በሥራ ላይ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን በማጣጣምና በማዋሃድ፣ የዘርፉን የመልማት አቅም አሟጦ በመጠቀም የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ እንዲያስችል ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያያበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ከዛሬ ሰኔ 19/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
5. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የከተማ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም ወጥቶ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት በሥራ ላይ በቆየው የከተማ ልማት ፖሊሲ በከተሞች የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት፣ ከተሞች በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ፣ አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ እንዲኾን፣ የገጠርና ከተማ፣ የከተማ ከተማ ትስስር እንዲጠናከር፣ መሰረተ ልማትና የተለያዩ ማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲስፋፉ በተደረገው ጥረት ውጤቶች የተመዘገቡ ቢኾንም ክፍተቶችም የነበሩበት ስለኾነ የነባሩን ፖሊሲ ክፍተቶች ለማረም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተሞች አካባቢ እየታዩ ያሉ አበረታች ለውጦችን ለማጽናት እና የበለጠ ለማጎልበት የከተማ ልማት ፖሊሲ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያያበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ከዛሬ ሰኔ 19 /2018 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
