በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል፡፡

25

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ ተቀብለው መግባታቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ገልጿል፡፡ ታጥቀው በጫካ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ውስጥ በዳንግላ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት የጤና ባለሙያ የነበረው እና በታጣቂዎች አደረጃጃት ስያሜ የቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ ብርጌድ የጽሕፈት ቤት ኀላፊ የነበረው አወቀ ባዬ ወደ ትግል የወጣው መስከረም 16/2018 ዓ.ም መኾኑን ተናግሯል፡፡ የሰላም አማራጭን የመረጠውም ትግሉ ዓላማ የሌለው በመኾኑ፤ ግለሰቦችን ወደ ማጥቃት እንዲሁም እርስ በእርስ መጠቃቃት ውስጥ በመገባቱ እና መንግሥት የሰላም አማራጭን በተደጋጋሚ በማሳየቱ እንደኾነ ገልጿል፡፡

የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ከገባ በኋላም የተለያዩ የተሃድሶ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ወደ ቀደመ የመንግሥት ሥራው መመለሱን ተናግሯል፡፡ ለዚህም መንግሥት ሆደ ሰፊ በመኾን ታጣቂ የነበሩትን ልዩ ውሳኔ ወስኖ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በማድረጉ አመሥግኗል፡፡

ታጥቆ ጫካ ላይ መንቀሳቀስ ለአካባቢው ሰላም ፋይዳ የለውም፣ በትጥቅ የሚፈታ ችግር የለም ያለው አቶ አወቀ ባዬ ወደ ሰላም መመለሳቸው ከራሳቸው አልፈው ለአካባቢያቸው፣ ለዞኑ እና ለክልሉ ፋይዳው የጎላ ነው ብሏል፡፡

አሁንም በጫካ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መንግሥት የሚያቀርበውን የሰላም አማራጭ እና ጥሪ ተጠቅመው እንዲመለሱ ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ቢሻው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ2018 በጀት ዓመት ታጥቀው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው መግባታቸውን ገልጸዋል።

የሰላም አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የአካባቢው የሰላም እና የልማት አቅም እንዲኾኑ የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ መኾናቸውንም አንስተዋል።

ቀድመው የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ መንግሥት ሥራቸው መመለሳቸውን ያነሱት ኀላፊው ቀሪዎቹ በተለያዩ የአካባቢ ጸጋዎች የሥራ ዕድል እየተመቻቸላቸው መኾኑንም አስረድተዋል።

ካለፉት ሦሥት ዓመታት ወዲህ በክልሉ እየተደረገ ያለው የእርስ በእርስ ግጭት የክልሉን ሕዝብ በሁሉም ዘርፍ ከማዳከም ያለፈ ያመጣው ለውጥ አለመኖሩን በመገንዘብ ሌሎች ታጣቂዎችም የሰላም መንገድን እንዲመርጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

#አሚኮ_ዜና #የሰላም_ጥሪ_የተቀበሉ_ታጣቂዎች #አማራ_ክልል

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ስንታየሁ

Previous article“የፍራፍሬ ልማት ውጤት የአርሶ አደሮችን አመለካከት ቀይሯል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔ አሳለፈ።