ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛነት ዕውቅና አሻራ ላስቀመጡት ፕሮፌሰር ዶናልድ ካርል የክብር ዶክትሬት ሰጠ።

9

 

ባሕርዳር፡ ሰኔ 18/2018ዓ.ም (አሚኮ)የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምሕርት መርሐግብሮች ያሠለጠናቸውን 4 ሺህ 83 ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።

በምረቃ መርሐግብሩ ለኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት የታሪክ አሻራ ላኖሩት ፕሮፌሰር ዶናልድ ካርል ጆሃንሰን የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷል።

ፕሮፌሰሩ በ1974 እ.ኤ.አ በአፋር ምድር ያገኟት የ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመቷ ድንቅነሽ የሰው ልጅ በሁለት እግሩ ቀጥ ብሎ መራመድ የጀመረው አእምሮው ከመገንባቱ በፊት መኾኑን በማረጋገጥ የዓለምን የሳይንስ ታሪክ የቀየረ ታላቅ ግኝት ነው ተብሏል። ይህ ግኝት ሳይንሳዊ እውነታን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የሰው ዘር በሙሉ መገኛና የጋራ ቤት መኾኗን በዓለም አቀፍ መድረክ በደማቁ እንድታውጅ አድርጎታልም ነው የተባለው።

​የዘንድሮውን የ2018 ዓ.ም የተማሪዎች ምረቃ ፕሮፌሰር ጆሃንሰን በዓለም አቀፍ ምርምር፣ በትምሕርትና የኢትዮጵያን የቅሪተ አካል ቅርሶች በመጠበቅና በማስተዋወቅ ላበረከቱት የዕድሜ ልክ ውለታ ይህ ከፍተኛ ተቋማዊ እውቅና እንደሚበረከተላቸውም ተገልጿል።

​ይህ የክብር ዶክትሪት ዲግሪ የፕሮፌሰሩን የላቀ ሳይንሳዊ አበርክቶ ማሰቢያ ብቻ ሳይኾን የዛሬዎቹ ተመራቂዎቻችንና ወጣት ተመራማሪዎች አድማስ ተሻጋሪ ለኾኑ የሳይንስ ግኝቶች እንዲተጉ የሚያነሳሳ ትልቅ የዕውቀት ፋና እንደኾነም ተጠቅሷል።

ታዋቂው ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሃንሰን በምረቃ መርሐግብሩ ላይ በዙም ቀጥታ መስመር በመግባት ለዕጩ ተመራቂዎች፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለበዓሉ ታዳሚዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ለተሰጣቸው ክብርም ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

#አሚኮ #አሚኮዜና #ጎንደር #universityofgindar #የተማሪዎችምርቃት

Previous article🎓 “ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ የተመሠረተ እና ለሕዝብ እየሠራ ያለ ተቋም ነው” የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደ ወይን (ዶ.ር)
Next article“በሁሉም እሴቶቻችን የተስፋ አምባሳደሮች ሁኑ” መቅደስ ዳባ (ዶ.ር)