🎓 “ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ የተመሠረተ እና ለሕዝብ እየሠራ ያለ ተቋም ነው” የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደ ወይን (ዶ.ር)

5

 

ጎንደር: ሰኔ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 4ሺህ 83 በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦሥተኛ ዲግሪ ሲያስተምራቸው የቆዩ ተማሪዎቹን አስመርቋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ተመራቂ ተማሪዎች፣ የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 56 የሚኾኑት ልዩ ልዩ የአካል ጉዳት ያጋጠማቸው ተማሪዎች መኾናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስራት አጸደ ወይን (ዶ.ር) አሳውቀዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ19ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ ከመደበኛ መማር ማስተማር ተግባሩ ባሻገር ሰፊ የማኅበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ተቋሙ በተለይ በጤናው ዘርፍ የኩላሊት እጥበት፣ የካንሰር ጨረር ሕክምና፣ የዐይን ሞራ ግርዶሽ እና መሰል የሕክምና አገልግሎቶችን ለአካባቢው ሕዝብ እየሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው በስኬት ጉዞ ላይ መኾኑን ያነሱት ዶክተር አስራት የዘንድሮው ተመራቂዎች በመውጫ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር በርካታ መኾናቸውን ገልጸዋል። ይህም ተቋሙ ለትምህርት ጥራት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መኾኑን አሳውቀዋል።

ተማሪዎች በቀጣይ የሥራ ዘመናቸው የጎንደር ከተማ ሕዝብ በቃል ኪዳን ቤተሰብ ተቀብሎ ያሳየውን ቤተሰባዊ ግንኙነት በየሄዱበት አካባቢ ሁሉ ማስፋት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብቁ እና ተወዳዳሪ በመኾን ቤተሰቦቻቸውን፣ ወገናቸውን እና ኢትዮጵያን በሙያቸው ማገልገል እንደሚገባቸውም ነው ያሳሰቡት።

#አሚኮ_ዜና #ጎንደር_ዩኒቨርሲቲ_ምርቃት #በአማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ፦ ኃይሉ ማሞ

Previous article“ተመራቂዎች በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ዘመናዊ ሥልጣኔን የምትገነቡ መኾን ይገባችኋል” ገጣሚ እና ፀሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ
Next articleጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛነት ዕውቅና አሻራ ላስቀመጡት ፕሮፌሰር ዶናልድ ካርል የክብር ዶክትሬት ሰጠ።