
ባሕር ዳር: ሰኔ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ለሰባተኛ ጊዜ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በቅድመ ምረቃ በ53 የትምህርት ክፍሎች እና በድህረ ምረቃ በ19 ትምህርት ከፍሎች 2 ሺህ 903 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው። ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 138ቱ ሴቶች ናቸው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ገጣሚ እና ፀሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአገው ሕዝብ በግንባታ፣ በግብርና፣ በባሕል እና በጥበብ የላቀ የሥልጣኔ ባለቤት ነው ብለዋል። ይህንን የዕውቀት መሠረት የያዘው ዩኒቨርሲቲው በትምህርት፣ በምርምር እና በባሕል ጥበቃ ላይ የሚያደርገው ትኩረት ተገቢ እና የሚደነቅ እንደኾነም ገልጸዋል።
ከውጭ የተቀዳው የዘመናዊ ትምህርት ሥርዓት ለሀገር ግንባታ፣ ለባሕል እድገት እና ለሕዝቦች አንድነት የተጠበቀውን ያህል ጉልህ አስተዋጽኦ አላበረከተም ነው ያሉት።
ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው የቀሰሙትን ዘመናዊ ዕውቀት በመጠቀም፤ ችግር ያለበትን የትምህርት ሥርዓት ወደ ሀገር በቀል እና እውነተኛ ልማትን ወደሚያመጣ መሠረት መቀየር ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታችሁ በርካታ ቁም ነገሮችን ተምራችሁ፣ ለዚህ ማዕረግ በቅታችኋል ነው ያሉት። ሥልጣኔን የምትናፍቁ ወጣት ምሁራን በመኾናችሁ በልዩነት ውስጥ አንድ ኾኖ ያሳደጋችሁን ማኅበረሰብ ባሕሉን ሳትዘነጉ እና ሳትከልሱ ማስቀጠል ይጠበቅባቹሀል ብለዋል።
ሀገር በቀል ዕውቀቱን ከኅብረተሰቡ ተቀብላችሁ ለቀጣዩ ትውልድ የምታሸጋግሩ መኾን አለባችሁ ነው ያሉት። “ተመራቂዎች በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ዘመናዊ ሥልጣኔን የምትገነቡ መኾን አለባችሁ” ብለዋል።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
