
ባሕር ዳር: ሰኔ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው።
በምረቃ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው
ብቃት እና አቅም ሁሌም የሚያድግ እና የሚሻሻል በመኾኑ ተመራቂዎች ሁሌም ለመሻሻል ዳግም ቃል የምትገቡበት፣ ተጨማሪ ኀላፊነት የምትረከቡበት ነው ብለዋል።
“በራሱ ላይ የሚሰራ ትውልድ ሀገርን ይሠራል” ተመራቂዎችም ራሳቸው ላይ በመሥራት እና በየጊዜው አቅማቸውን በማሻሻል ለማኅበረሰቡ ስኬት እና እድገት እንዲሠሩ፤ ማኅበረሰባቸውን እና ሀገራቸውን በማገልገል ውለታ ከፋይ እንዲኾኑ አስገዝበዋል።
ተመራቂዎች በቀጣይ ሕይወታቸው ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር አላምደው በአመለካከት ራሳቸውን ገንብተው በሚሠማሩበት የሥራ መስክ ሀገራቸውን እና ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
መንግሥት ሰባቱን የጉባ ብስራቶች ይፋ ባደረገበት ወቅት መመረቃቸው ተመራቂዎች የሀገራቸውን ብሔራዊ አጀንዳዎች ከግብ እንዲደርሱ ኀላፊነት ያለባቸው መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ቋሚ መሪም ኾነ ቋሚ ትውልድ የለም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው መሪ እና ትውልድ በቅብብሎሽ እየተተካ የሚቀጥል ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ የተረከባት ሀገር በርካታ እዳዎች ያለባት ሀገር በመኾኗ እዳዋን ለመቅረፍ ምንዳዋን እንደ ወረት በመጠቀም ለሀገራቸው እድገት ትኩረት ማድረግ ከተመራቂዎች ይጠበቃል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በእድገት ጎዳና ላይ ናት ያሉት አቶ ቴዎድሮስ
ምክንያታዊ በመኾን ሀገራችን ያሉባትን ችግሮች በውል በመረዳት ለሀገር እድገት ሁነኛ ድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።
እያንዳንዱ ተመራቂዎች የሀገር እድገት፣ ልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
#አሚኮ #እንጅባራ-ዩኒቨርሲቱ #የተማሪዎች_ምረቃ
