🎓 “ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው የገበያችሁትን ዕውቀት ተጠቅማችሁ ሀገር እና ወገናችሁን ማገልገል ይጠበቅባችኋል” ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር)

42

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለሰባተኛ ጊዜ ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ዛሬ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 2 ሺህ 903 ተማሪዎች እያስመረቀ እንደኾነ ተናግረዋል። በ2018 ዓ.ም ካስፈተናቸው የመደበኛ እና የተከታታይ መርሐ ግብሮች ተማሪዎች መካከል በአማካይ 87 ነጥብ 4 በመቶ በላይ ተማሪዎችን በሀገር አቀፍ መውጫ ፈተና ማሳለፉንም ጠቅሰዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በአራት መርሐግብሮች (በአንስቴዥያ፣ በሶፍትዌር ምሕንድስና፣ በመምህራን ትምህርት ካሪኩለም ጥናት እና በአገዎኛ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ) መርሐግብር የሚያስመርቅ መኾኑ ካለፉ የምረቃ መርሐግብሮች ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በአገውኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ ትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስመረቅ በሀገር ደረጃ የመጀመሪያ እንደኾነም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በ2018 የትምህርት ዘመን 14 ሺህ 400 በላይ ተማሪዎችን በ59 የቅድመ ምረቃ መርሐግብሮች፣ በ47 የሁለተኛ ዲግሪ መርሐግብሮች እና በ5 የሦሥተኛ ዲግሪ መርሐግብሮች በድምሩ በ110 መርሐግብሮች የማስተማር ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከመማር ማስተማር ተግባር ባሻገርም በማኅበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱንም ገልጸዋል። አሁን ላይ ከ43 የሀገር ውስጥ እና ከ21 የውጭ ሀገር ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የዛሬ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው የገበዩትን ዕውቀት ተጠቅመው ሀገር እና ወገናቸውን በማገልገል የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ አምባሳደር እንዲኾኑ ፕሬዝዳንቱ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

#አሚኮ_ዜና #የእንጅባራ_ዩኒቨርሲቲ_ምርቃት #በአማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

Previous articleየክረምት በጎ አድራጎት – ሀገራዊ አብሮነታችን በተግባር የገለጠ ብርቱ ሼል!
Next article“በራሱ ላይ የሚሠራ ትውልድ ሀገርን ይሠራል” አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው