
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ሀገር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰብዓዊነትን፣ ቅን ልቦናን እና ውብ እጆችን ለጋራ ዓላማ የምናስተሳስርበት ልዩ ተግባር ነው። ይህ ተግባር በቁጥር ወይም በውጤት መጠን ብቻ የሚለካ ሳይኾን የህሊና እፎይታን በሚሰጥ እና አብሮነትን በሚያጠናክር መንፈስ የሚከናወን የኢትዮጵያ ገናና እሴት ነው።
ቀደም ሲል ክረምት ሲመጣ ለአቅመ ደካሞች እና አረጋውያን የነበረው ትዝታ አስከፊ ነበር። ጠያቂ የሌላቸው ወገኖች ሰማዩ ሲጠቁር ልባቸው ይሸበር ነበር። የቤታቸው ጣራ ሲያፈስ በቁሩ ሲጨነቁ ያድሩ የነበረበትን ጊዜ አሁን በትዝታ መልክ ያነሱታል።
ዛሬ ግን ነገሮች ተቀይረዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ባሕል ሥር በመስደዱ ወገኖች በብሔር፣ በሃይማኖት እና በማንነት ሳይከፋፈሉ አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ ሲረባረቡ ማየት የተለመደ ነው። የአረጋውያን ቤት ይታደሳል፤ ችግኝ ይተከላል፤ ወጣቶች ደም በመለገስ የሌላውን ሕይወት ይታደጋሉ።
ከዚህ በፊት “ክረምት መጣ” ብለው ይጨነቁ የነበሩ አቅመ ደካሞች፣ ዛሬ በሰላም አድረው ሀገርን መመረቅ እና ሰላምን መስበክ ችለዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሚታየው ከፍተኛ የዜጎች ተነሳሽነት፣ በተለይም የወጣቶች ተሳትፎ የነገዋን ኢትዮጵያ በገዛ እጃቸው ለመጻፍ የሚያደርጉት ጥረት ማሳያ ነው። ይህ መልካም ተግባር የሀገር መሪዎችን ጭምር ያሳተፈ የላቀ የኅብረት ባሕል ኾኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዕቅድ ታቅዶ እንዲተገበር እያደረጉ ይገኛሉ።
በተለያዩ አካባቢዎችም ተግባሩ እየተከናወነ ይገኛል። ይህ በጎ ተግባር ለሀገር በጋራ ክንድ መሥራትን እና መተጋገዝን አጉልቶ የሚያሳይ ሀገራዊ ተግባርም ነው።
በተለይም በዘንድሮው ክረምት ወጣቶች ዕውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን፣ ባለሃብቶች ሀብታቸውን፣ ተቋማት ያላቸውን አቅም በማዋጣት የአቅመ ደካሞችን ቤት በመገንባት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎችም ተግባራት መሳተፍ ይገባቸዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአካላዊ ግንባታዎች ባሻገር ወደ አዕምሯዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ለውጥ የሚያሻግር ድልድይም ነው። ይህ “ለሰው ሰው ነው ልብሱ” የተባለለት መልካም ተግባር ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ አጋምዶ የቆየ ነው።
ለነገም የተሰናሰለ አብሮነት ለማጋመድ ተሰንቋል። የሰው ልጅ በጎነትን እና ደስታን ከሌላው ፊት ሲመለከት ከሚያገኘው እርካታ በላይ የሚበልጥ ነገር የለምና።
ስለዚህ ይህንን መልካም ባሕል እንደ ሀገር ለማስቀጠል የተግባር ዘመቻው የወጣቶች ብቻ ሳይኾን የሁላችንም የጋራ ግዴታ ነው። ሁላችንም እጃችንን በመዘርጋት ከዚህ የመልካምነት ተጋድሎ ማዕድ ተቋዳሽ መኾን ይገባል።
#አሚኮ_ዜና #የበጎፈቃድ_ሥራ #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
