
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ግንባታ እና ለተረጋጋ ሰላም የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና እጅግ ወሳኝ ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ሰሎሞን አየለ በኢትዮጵያ ሀገር እና ሕዝብን በማስቀደም ሰለማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የጋራ ምክር ቤቱ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ከምርጫ በፊት እና በምርጫ ቀን የተለያዩ ሥራዎችን ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። ከምርጫ ባሻገርም ሀገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲኾን በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአንድ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመትከል ሰላማዊ ምርጫ አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎችም ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ታሪካዊ አሻራ አሳርፈዋልም ብለዋል። የዴሞክራሲ ባሕል እንዲጎለብትም ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ነው ያሉት።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፈም መራጩ ሕዝብ ምንም ሳይገድበው የራሱን ኀላፊነት የተወጣበት እና ትልቅ የዴሞክራሲ ልምምድ አሻራ ያስቀመጠበት ሁኔታ እንደተፈጠረም ጠቅሰዋል።
ከምርጫ በኋላም በሀገር ደረጃ የተወዳደሩ 42 የፖለቲካ ፖርቲዎች በጥብቅ ሥነ ሥርዓት የሕዝቡን ድምጽ አክብረው የተቀበሉበት መንገድ እና አሉን ያሏቸውን ቅሬታዎች ያቀረቡበት መንገድ እንዳለ ገልጸዋል። ይህም ሕግ እና ሥርዓትን እየተከተሉ የመምጣት ማሳያ ነው ብለዋል። ምርጫው በሰላም መጠናቀቁም ትልቅ ግብ እንደኾነም ተናግረዋል።
እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወካዮች ምክር ቤት እና ክልል ምክር ቤት ላይ ወንበር ማግኘት ችለዋልም ነው ያሉት።
በሕዝብ ድምጽ አሸናፊ የኾነ ፓርቲም ኾነ ያላሸነፈው ፓርቲ ሕዝብ የሰጠውን ድምጽ ማክበር እንደሚጠበቅበት አንስተዋል። ሕዝብ ትልቅ አደራ ሰጥቷል፤ ይሄን አደራ በአግባቡ መወጣት ያስፈልጋል ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሀገራዊ መድረኮችን በማዘጋጀት በምርጫ ሂደቱ እና የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ሠፊ ሥራ ሠርቷል ያሉት ኀላፊው በቀጣይም በሰላም ጉዳይ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል። የሰላም ጉዳይ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ የሚመራው አካል ብቻ ሳይኾን የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅም አንስተዋል።
የፖለቲካ ሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም ሕዝብ በሰላም ወጦ በሰላም እንዲገባ የውስጥ እና የውጭ ሰላምን በጋራ ማስጠበቅ የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ እንደሚቆሙም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
