“ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ከምርጫ ውጭ ላሉ የኃይል አማራጮች ፍላጎት እንደሌለው ያሳየበት ትልቅ እሴት ነው” የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር

4

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት አከናውናለች። የብልጽግና ፓርቲ መንግሥት መመሥረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ ማግኘቱንም ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የሕዝብ ውክልና ይዘው የምክር ቤት መቀመጫዎችን አግኝተዋል። ይህ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎች ወንበር ማግኘት ለሀገሪቱ የቀጣይ ፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ፤ ሰላም እና ደኅንነት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ምሁራን ይገልጻሉ።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት መምህር ሀሳቡ ተስፋ ይህ ውክልና የሀሳብ ብዝኃነትን ያስተናግዳል ብለዋል። የፖለቲካ ምህዳሩም ይበልጥ አካታች፣ ነጻ እና የበሰለ እንዲኾን ያግዛል ነው ያሉት። አሠራሩ ለሀገሪቱ ሰላም እና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ወሳኝ እንደኾነም ገልጸዋል።

የሥልጣን ምንጭ ምርጫ ብቻ መኾኑን ማረጋገጥ የሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫ ነው። ይህም በሥልጣን ጉዳይ ላይ የሚነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትልቅ ዋስትና ይኾናል ብለዋል።

በሰባተኛው ምርጫ አካታች የመኾን ጥረትም ትልቅ እርምጃ መኾኑን አንስተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠረው ሕዝብ ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ ኾኖም ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል ነው ያሉት። ይህ ከፍተኛ ተሳትፎ ሕዝቡ ከምርጫ ውጭ ላሉ የኃይል አማራጮች ፍላጎት እንደሌለው ያሳየበት ትልቅ እሴት እንደኾነ ነው የገለጹት።

የሕዝብ ውክልና በምክር ቤት መኖሩ የተለዩ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች በሕጋዊ መድረክ እንዲነሱ ያስችላል፤ በዚህም ምክንያት “በኃይል ካልኾነ አይኾንም” የሚሉ አካላት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጡ ያደርጋል ብለዋል።

አዲሱ መንግሥት የተጣለበትን አደራ ለመወጣት ቁርጠኛ መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል። መንግሥት እስካሁን ከተሄደበት መንገድ በተሻለ አዳዲስ አቀራረቦችን ማሳየት እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል።

ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጊዜ ባይፈቱም እንኳን ያሉትን ችግሮች ዕውቅና መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል። መንግሥት ችግሮችን በሚችለው ልክ ለመፍታት በቅንነት መሥራት እና ሕዝብን ያሳተፈ የጋራ መፍትሔ መፈለግ ለሰላም ግንባታው ዋነኛ መሠረት ናቸው ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ አየር መንገድ ከባሕር ዳር – ደብረ ማርቆስ መደበኛ በረራ ሊጀምር ነው።
Next article“በሀረሪ ክልል የቱሪዝም ዘርፉን የሚያጎለብቱ የኢንቨስትመንት ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ