
አዲስ አበባ: ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሁለት ቀናት የሚቆይ ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ የሣይበር ደኅንነት ማኅበር ፕሬዝዳንት ብርሃኑ በየነ (ዶ.ር) የሣይበር ደኅንነት ዓለምአቀፍ ወቅታዊ ትኩረት እንደመኾኑ ጉባኤው በትክክለኛው ጊዜ የተጀመረ ነው ብለዋል።
ይህ ጉባኤ በአፍሪካ ደረጃ ዕውቀትን ለመለዋወጥ፣ በተግባር የታዩ የሣይበር ጥቃት መከላከያ ተሞክሮዎችን ለማካፈል እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዙ የደኅንነት መፍትሔዎችን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሣይበር ጥቃት ሠለባ እየኾኑ በመኾናቸው የመረጃ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እና የሠው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን አስቀድሞ በደኅንነት መዋቅር ላይ መመስረት ምርጫ ሊኾን እንደሚገባ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ፕሮግራም ምክትል አስተባባሪ ማማ ኬይታ የሣይበር ደኅንነት እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት የአፍሪካንም ኾነ የዓለም አቀፍ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሣኝ መሣሪያዎች ናቸው ብለዋል።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ ትልቅ ተስፋን ይዞ የመጣ ቢኾንም የራሱ ስጋቶች እንዳሉት የገለጹት አስተባባሪዋ ይህንን ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት ለማዋል የራስን መረጃ በራስ የመቆጣጠር እና የመረጃ ሉዓላዊነት አቅምን ማሣደግ ይገባል ነው ያሉት።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሃሚድ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። ከቴክኖሎጂው ዕድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የሳይበር ደኅንነት ስጋቶችን ለመከላከል ጠንካራ መዋቅር መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሳይበር ጥቃቶች ድንበር ተሻጋሪ በመኾናቸው፣ በሀገር ውስጥ ያሉ ተቋማት እና የአፍሪካ ሀገራት በጋራ በመተባበር መረጃዎችን እና ተሞክሮዎችን መለዋወጥ እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥተዋል።
የሀገሪቱን ወሳኝ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ከጥቃት መከላከል እና የዲጂታል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለብሔራዊ ደኅንነት ወሳኝ በመኾኑ ተቋሙ ይህንን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ግብርና መር ኢኮኖሚ የምትከተል ሀገር እንደመኾኗ ዘርፉን ከቴክኖሎጂ እና ከዓለም አቀፍ የሣይበር ደኅንነት ፓሊሲ ጋር የተናበበ ለማድረግ ተግባራዊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
#አሚኮ ዜና #Cyber_Security_Conference
#Addis Ababa
ዘጋቢ መሠረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
