🎑ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምን ለውጥ አመጣች?

5

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ያለፉት አምስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት የተደረገባቸው እና አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡባቸው ነበሩ።

እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የወጭ ንግድን ለማሳደግ እና ምርትን ለመተካት በርካታ ስትራቴጂካዊ ሥራዎችን አከናውኗል። ከተከናወኑ ዋና ዋና የግብርና ሥራዎች እና ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከልም የሰብል ምርታማነት እና የሌማት ትሩፋት ይጠቀሳሉ።

ባለፉት አምስት ዓመታት በዋና ዋና የሰብል ምርቶች🎑 (በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ እና መሰል ሰብሎች) ላይ ከፍተኛ የምርት ዕድገት ታይቷል። የበጋ ስንዴ መስኖ ልማትም ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገበ ትልቁ ስኬት ነው። ይህም ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከውጭ ታስገባ የነበረውን የስንዴ ፍጆታ በመቀነስ የወጭ ቅነሳ ላይ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አነስተኛ የእርሻ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች መሬታቸውን በኩታ ገጠም በማጣመር እና በጋራ ሜካናይዜሽንን (ትራክተር እና ኮምባይነር) እንዲጠቀሙ በማድረግም ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ላይ ያገኘነው መረጃ ይገልጻል።

የግብርና ሥራ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የተመጣጠነ የምግብ ሥርዓትን ለመገንባትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀረጸው 🐄🐓 የሌማት ትሩፋት (የእንስሳት እና ተዋጽኦ ልማት)ንቅናቄ ባለፉት 3 እና 4 ዓመታት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። በዘመናዊ የወተት ላሞች ዝርያ ማሻሻል እና በከተማ ግብርና አማካኝነት የወተት ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

የገቢ ምንጫቸው አነስተኛ ለኾኑ አርሶ አደሮች እና ወጣቶች የዶሮ ጫጩቶችን በማሰራጨት የእንቁላል እና የዶሮ ሥጋ አቅርቦት እንዲጨምር ተደርጓል። ዘመናዊ ቀፎዎችን በማሰራጨት እና ሰው ሠራሽ የዓሳ ማራቢያ ኩሬዎችን በስፋት በመሥራት ረገድም ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ሌላው በአምስት ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቶት የተሠራው እና ውጤት የተመዘገበበት የግብርና ሥራ የገበያ እና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶች (የአረንጓዴ አሻራ እና የልማት ኮሪደር) ማምረት ነው። የኢትዮጵያ ቀዳሚ የውጭ ምንዛሬ አምጭ የኾነው ቡና ባለፉት አምስት ዓመታት የጥራት እና የይዘት ማሻሻያ ተደርጎበት ወደ ውጭ የሚላከው መጠን እና የተገኘው ገቢ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል።

🥑🌱የአቮካዶ ዝርያን በስፋት በማምረት ወደ አውሮፓ ገበያ የመላክ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታም አድጓል። በሻይ ቅጠል እና በአበባ ልማትም የግል ባለሀብቶችን በማበረታታት የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

🚂በቴክኖሎጂ እና በግብዓት አቅርቦትም ዕድገት ተመዝግቧል። መንግሥት የግብርና መሣሪያዎችን (ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮች እና የውኃ ፓምፖች) ከቀረጥ ነፃ በኾነ ሥርዓት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ማደረጉ የግብርናውን ዘመናዊነት አፋጥኖታል። በዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት የማዳበሪያ ዋጋ መናር እና የሎጂስቲክስ መዘግየት ፈተናዎች ቢኖሩም አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ እና አዳዲስ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት ጥረቶች ተደርገዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት ወደ መስኖ ልማት፣ ከባሕላዊ ወደ ሜካናይዜሽን እርሻ እና የምርት ሥብሠባ የተሸጋገረበት ስትራቴጂካዊ ለውጥ ታይቷል።

የአየር ንብረት መለዋወጥ (ድርቅና ጎርፍ)፣ የሰላም እና መረጋጋት እጥረት በየአካባቢው መፈጠሩ እና የግብርና ግብዓቶች (ማዳበሪያ እና ኬሚካል) ዋጋ መጨመር ግን ዘርፉ ሙሉ አቅሙን እንዳይጠቀም አሁንም ፈተናዎች ናቸው። ነገር ግን እነዚህን ፈተናዎች በመቋቋም በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ለውጥ መጥቷል።

#አሚኮ_ዜና #በአምስት_ዓመቱ_የግብርናው_ዕድገት #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ጸጋዎቿን እየገለጸች ቱሪዝሟን እያሳደገች ነው።
Next articleየዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው።