ኢትዮጵያ ጸጋዎቿን እየገለጸች ቱሪዝሟን እያሳደገች ነው።

4

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የቱሪዝም ባለጸጋ ናት። ዕምቅ ሀብት ያላት ኢትዮጵያ ይህን ሀብቷን ለዓለም የሚገልጥ ጠፍቶ ደብዝዛ ቆይታለች። አሁን ላይ ዘመን እየተለወጠ ሃብቶቿ እየተገለጡ ናቸው።

ኢትዮጵያ የተከደነው ውበቷ ሲታይ፤ ያረጁ ታሪካዊ ቅርሶች ሲታደሱ እና አቧራ የጠጣው ጸጋዋ ሲለወጥ በዐይናችን እያየን ነው።

መንግሥት ቱሪዝምን እንደ አንድ ተራ የኢኮኖሚ ዘርፍ ብቻ ሳይኾን ለሀገረ መንግሥት ግንባታ፤ ለወል ትርክት መጠናከር እና ለዜጎች የእርስ በእርስ መቀራረብ እንደ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ መሣሪያ አድርጎ እየሠራበት ነው።

“በገበታ ለሸገር”፣ “በገበታ ለሀገር” እና “በገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች አማካኝነት ሀገሪቱ ያሏትን የተበታተኑ ሀብቶች አስተሳስሮ ለዓለም በማቅረብ የኢትዮጵያን ክብር እና ዝና መልሶ መገንባት ተችሏል።

በዚህም ጎርጎራ፣ ሎጎ ሐይቅ፣ ወንጭ፣ ኮይሻ፣ ሐላላ ኬላ እና ጨበራ ጩርጩራ ተገልጠው አካባቢን የጠበቁ እና የሀገር ገጽታን የቀየሩ ዘመናዊ መዳረሻዎች ኾነዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የውጭ ሀገር ቱሪስት ፍሰት በ2014 በጀት ዓመት 781 ሺህ ነበር። በ2017 በጀት ዓመት ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከፍ ማለቱ የዚሁ የለውጥ ፍሬ ነው።

የአንድነት ፓርክ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ 14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ጎብኚዎችን በማስተናገድ 1 ነጥብ 48 ቢሊዮን ብር ገቢ አስገኝቷል።

ኢትዮጵያ በአዲሱ የቱሪዝም ስልት የማይስ ቱሪዝም ላይ በስፋት ሠርታለች። በተለይም በዚህ ዘርፍ የታላቁ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በርካታ የኮንፈረንስ ጎብኝዎችን አስተናግዶ ጠቅም ያለ ገቢ አስገኝቷል። የኢትዮጵያ እና የኢትጾጵያውያን ታሪክም በሚገባው ልክ ተዋውቆበታል።

በቱሪዝም የተሠራው ሥራ የሆቴሎችን የዕንግዳ መቀበል ምጣኔን ወደ 75 በመቶ ከፍ እንዲል በማድረግ ሰፊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን እና ለወጣቶች እና ሴቶች የሥራ ዕድልን ፈጥሯል።

ሌላው እና ቱሪዝሙን ከፍ ካደረጉት ሥራዎች ውስጥ የኮሪደር ልማት ይጠቀሳል። ይህ ሀገራዊ የቱሪዝም እና የገጽታ ግንባታ ንቅናቄ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ብቻ የተገደበ ሳይኾን በክልል ከተሞች ጭምር በተግባር እየተንጸባረቀ ይገኛል።

ለአብነት በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ፣ በወልድያ እና በሌሎች ከተሞች የተሠሩ ሥራዎች የከተሞችን የቱሪስት መስብዕነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ ሥራዎች ናቸው።

ከተፈጥሮ መስህቦች ባሻገር የሀገሪቱን ስፖርታዊ ቱሪዝም ለማነቃቃት እና ታሪካዊ ቅርሶችን ከዘመናዊ መሰረተ ልማት ጋር አጣምሮ ለመጓዝ የተጀመሩት እና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙት የባሕር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየምን ጨምሮ ሌሎች የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለዘርፉ ለተሰጠው ትኩረት ማሳያዎች ናቸው።

እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች እና ስፖርታዊ ማዕከላት መበልጸግ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ከማሳደጉም በላይ የክልሉን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በአዲስ ጉልበት እያነቃቁትም ይገኛሉ።

ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እና የኮንፈረንስ ማዕከልን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንዳሉት ትራንስፎርሜሽን የአንድ ጊዜ ክስተት ሳይኾን ሂደት ነው። ለዚህም ሐቀኝነት፣ ጽናት እና ከልምድ መማርን ይጠይቃል፣ በቱሪዝሙ ዘርፍም የተሄደው ርቀት የዚሁ ጽናት ውጤት ነው።

በአንድ ዓመት ውስጥ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማስተናገድ አዲስ አበባ የኮንፈረንስ እና የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን እንድታጸና በተግባር ማረጋገጥ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ጸጋዎችን በአግባቡ ሲገለጡ ታሪኳ የጥል መነሻ መኾኑ ቀርቶ የውበት፣ የገቢ እና የኩራት ምንጭ ይኾናል። እየኾነም ነው። አሁን ላይ የዓለም የስብዐት ማዕከል ኾናለች።

#አሚኮ_ዜና #ቱሪዝም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ዕቃ ጫኝ መርከብ የሆርሙዝን ሰርጥ አቋርጣ ወደ ጅቡቲ እየተጓዘች ነው።
Next article🎑ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምን ለውጥ አመጣች?