የኢትዮጵያ ዕቃ ጫኝ መርከብ የሆርሙዝን ሰርጥ አቋርጣ ወደ ጅቡቲ እየተጓዘች ነው።

3

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) MV ጊቤ የሚል መጠሪያ የኢትዮጵያን ንንደቅ ሰቅላ የምትንቀሳቀሰው መርከብ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በተነሳው ጦርነት ሳቢያ ለወራት በሆርሙዝ ሰርጥ ቆመው ከነበሩ መርከቦች መካከል አንዷ ናት። መርከቧ የሆርሙዝ ሰርጥን አቋርጣ ወደ ጅቡቲ ወደብ እየገሰገሰች መሆኗን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል።

‘ጊቤ’ በአሁኑ ወቅት በኦማን ገልፍ አካባቢ እንደምትገኝ የተነገረ ሲሆን፤ ከአራት ቀናት በኋላ ጅቡቲ ወደብ እንደምትደርስ ይጠበቃል።

አሜሪካ እና እስራእል ከኢራን ጋር በገቡበት ጦርነት ሳቢያ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ የነበረው የመርከቦች እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ በዓለም ሀገራት ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያስከትል መቆየቱ ይታወሳል። ኢትዮጵያም በተለይም በነዳጅ ምርት እና በሌሎች ሸቀጦች በኩል የሚደርሱ ተጽእኖዎችን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስም በሆርሙዝ ሰርጥ አካባቢ የነበረውን ውጥረት ተቋቁመው ሀገራዊና ሙያዊ ክብራቸውን በማስጠበቅ ሲሠሩ ለቆዩ መርከበኞች ምስጋናውን አቅርቧል።

አሁን ላይ በሀገራቱ መካከል እየታየ ያለው ንግግር ተግባራዊ ኾኖ ችግሩ በዘላቂነት እንደሚፈታ፣ የሚዘጋና የሚከፈተው የሆርሙዝ ሰርጥም ለእንቅስቃሴ ነጻ እንደሚኾን ሀገራት በጉጉት የሚጠብቁት ጉዳይ ነው።

#አሚኮ #አሚኮዜና #ባሕርዳር #ሆርሙዝ #ኢትዮጵያ

Previous articleሩሲያ ለሰላም ንግግር ዝግጁነቷን አስታወቀች።
Next articleኢትዮጵያ ጸጋዎቿን እየገለጸች ቱሪዝሟን እያሳደገች ነው።