
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር የገቡበትን ጦርነት ለመቋጨት እና ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
ዘኢንዲፔንዳት እንዳስነበበው ከኾነ ይህ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ውሳኔ የተሰማው ዩክሬን በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያዎች ላይ ባደረሰችው ጥቃት የነዳጅ እጥረት ከተከሰተ ከቀናት በኋላ ነው።
ፑቲን የዩክሬንን ጥቃት ሕዝቡን ለመጉዳት የተደረገ ተንኮል ሲሉ ፈርጀውታል። ሩሲያ ቀደም ሲል በኢስታንቡል በተደረሱት ስምምነቶች መሠረት ለመደራደር ዝግጁ መኾኗን ገልጸዋል። ይህንን ስምምነት በወቅቱ የጀመረው የዩክሬን ልዑክ መኾኑንም አስታውሰዋል።
በወቅቱ ከሁለቱም ወገን የተወከሉ ተደራዳሪዎች ሁሉንም በከባድ ሁኔታ የቆሰሉ ወታደሮችን ጨምሮ ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የተማረኩ ተዋጊዎችን በሙሉ ለመለዋወጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩክሬን መልዕክተኛ አንድሪ ሜልኒክ ትዕግስታቸው ማለቂያ የሌለው መኾኑን ተናግረዋል። ጦርነቱን ለማቆም ጠንካራ ዓለም አቀፍ ግፊት ካልተደረገ ኪየቭ አሁን ያለውን የተኩስ አቁም የውሳኔ ሐሳብ ልትከልስ እንደምትችልም ገልጸዋል።
ፑቲን በበኩላቸው የኪየቭ አገዛዝ ሊደረጉ ከሚችሉ ድርድሮች በፊት ጠንካራ አቋም እንዳለው ለማስመስከር እየሞከረ ነው ብለዋል። በጦር ሜዳው ላይ ያለው እውነታ ፍጹም የተለየ መኾኑን እና የሩሲያ ወታደራዊ ክፍሎች በየቀኑ ወደፊት እየገፉ መኾኑን ገልጸዋል።
ከቀናት በፊት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ለፑቲን ግልጽ ደብዳቤ በመላክ ጦርነቱን ለማቆም ፊት ለፊት የሚገናኙበት የሁለትዮሽ ስብሰባ እንዲደረግ ሀሳብ አቅርበው ነበር።
ዘለንስኪ ፑቲንን በፈረንሳይ በሚካሄደው የቡድን 7 ጉባኤ ላይ ለማግኘት ሀሳብ አቅርበውም ነበር። ነገር ግን በወቅቱ ሩሲያ ለመነጋገር ዝግጁ አልነበረችም።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን እና በሩሲያ መሪዎች መካከል የሁለትዮሽ ስብሰባ እንዲደረግ የሚለውን ሀሳብ ደግፈውታል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
