
ሁመራ: ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሕወሓት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ሀገሪቱን ወደ ጦርነት ለመምራት እየሠራ መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር አስታውቋል፡፡
ጦርነትን ወደ ዘላቂ ሰላም ለመመለስ በሚደረጉ የሰላም ስምምነት ድንጋጌዎች ላይ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀል እና መልሶ ማቋቋም (ዲዲአር) ዋነኛው ተግባር መኾኑን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ያነሳሉ።
የፕሪቶሪያ ስምምነትም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የነበረውን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም የተደረገ የሰላም ስምምነት ነው።
ይህንን ጦርነት በማስቆምም የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ መቀላቀል እና ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም የሚሉት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተካሄደው ስምምነት ዋንኛ ነጥቦች መኾናቸፍውን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር አባላት አንስተዋል፡፡
የዚህ ስምምነት ሀሳብ በአንቀጽ ስድስት ላይ በግልጽ የተቀመጠ ቢኾንም ሕወሓት ከመጀመሪያው ጀምሮ ስምምነቱን እንዳፈረሰው የማኅበሩ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ገሠሠው ወንድም (ዶ.ር) ያስረዳሉ።
ሕወሓት የሁለቱ ተደራዳሪ አካላት የሰላም ስምምነት ዋነኛ መርህ የኾነውን የሁለትዮሽ አሸናፊነት መርህን መጣሱን የተናገሩት ደግሞ የማኅበሩ አባል አቶ እያቸው ተሻለ ናቸው፡፡ ቡድኑ በስምምነቱ “እኔ ነኝ ያሸነፍኩት” በሚል መሠረተ ቢስ ፕሮፖጋንዳ ስምምነቱን በተግባር ማፍረሱንም አክለው ገልጸዋል።
የትግራይ ሕዝብ የሰላም አማራጭን በመከተል የአጥፊ ቡድኑ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይኾን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም የማኅበሩ አባላት ጥሪ አቅርበዋል።
ሕወሓት የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው ወደ ኀይል አማራጭ ለመግባት የሚያደርገው ሙከራ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጣ ጥቃት መኾኑን መገንዘብ እንደሚገባም አባላቱ ጠቅሰዋል።
#አሚኮ_ዜና #የሰላም_ሥምምነት #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
