አሚኮ እና የማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ።

5

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

በፊርማ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ አሚኮ በብዙ ቋንቋዎች አገልግሎት እየሰጠ፣ ተደራሽነቱን እያሰፋ የሚገኝ ትልቅ የሚዲያ ተቋም ነው ብለዋል።

በተለያዩ ቋንቋዎች ከሚያስተላልፋቸው የቴሌቪዥን ሥርጭት ባለፈ በሬድዮ፣ በጋዜጣ እና በዲጂታል ሚዲያ አማራጮች ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ እየኾነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

አሚኮ እና የማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ተልዕኳቸው የተለያየ ቢኾንም የሚያገለግሉት ለአንድ ሕዝብ በመኾኑ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በሁለቱ ተቋማት የተፈረመው ስምምነት የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ እንደ መነሻ የሚያገለግል ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።

በሥምምነቱ መሠረት አሚኮ ባሉት የሚዲያ አማራጮች የማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ፣ የተቋሙ ብራንድ እንዲተዋወቅ፣ ገጽታው እንዲገነባ፣ ትርፋማ እንዲኾን እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዘላለም በላይ የማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታየውን የቴክኖሎጂ ፍላጎት፣ የአቅርቦት እና የአጠቃቀም ክፍተቶችን ለመፍታት፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከአሚኮ ጋር ለመሥራት ስምምነት መፈራረሙ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የተቋሙን የብራንዲንግ ሥራዎች ከፍ ባለ መንገድ ለማስተዋወቅም ትልቅ መደላድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

ተቋሙ የሚያመርታቸውን ምርቶች ለማስተዋወቅ እና የገበያ አቅም እንዲፈጠር ምቹ እንደሚኾንም አንስተዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕወሓት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በአደባባይ ጥሷል” የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር