የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ።

4

 

አዲስ አበባ: ሰኔ 16/2018 (አሚኮ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የ11 ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል።

አዲስ የተሾሙ አምባሳደሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቃባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫና ማስተናገጃ በመኾኗ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት።

ለፕሬዚዳንቱ አዲስ የሹመት ደብዳቤያቸውን ያስረከቡት አምባሳደሮች፣አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመኾኗ ያላትን አህጉራዊ የዲፕሎማሲ መዲናነት አድንቀዋል። ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የታየውን የልማት እመርታም በቅርብ መታዘባቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደሮቹ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

በተለይም በንግድ ልውውጥ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኢነርጂ፣ በውኃ ሀብት አሥተዳደር፣ በቱሪዝም እና በባሕል ዘርፎች ላይ አዳዲስ የትብብር ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሠሩ አስረድተዋል።

ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ መድረኮችን መጠቀም ዋነኛ ትኩረታቸው እንደኾነ ነው የጠቆሙት።

አምባሳደሮቹ በቅርቡ የተጠናቀቀውን 7ኛውን አጠቃላይ ምርጫ ስኬት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከአፍሪካ ሀገራት የተወከሉ ዲፕሎማቶች፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና መሰል አህጉራዊ ተግባራት እያከናወነች ያለችውን ሚና ማድነቃቸውን አምባሳደር ነቢያት ተናግረዋል።

የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንት ታዬ ያቀረቡት የሳዑዲ አረቢያ ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ፣ የፖርቱጋል፣ የናይጄሪያ፣ የስሪ ላንካ፣ የማላዊ፣ የጋና፣ የኡራጓይ፣ የኡዝቤክስታን፣ የስሎቫክያ እና የማዳጋስካር አምባሳደሮች ናቸው።

ዘጋቢ: ቴዎድሮስ ኅይለኢየሱ

#አሚኮ #ፕሬዝዳንት_ታዬ #ሹመት #ዲፕሎማት#ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ወቅት ባሻገር ከሕዝቡ ጋር የሚገናኙበት ቋሚ መድረክ ሊኖራቸው ይገባል።