የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ወቅት ባሻገር ከሕዝቡ ጋር የሚገናኙበት ቋሚ መድረክ ሊኖራቸው ይገባል።

3

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ያካሄደውን የጠቅላላ ምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። ብልጽግና ፓርቲ በአብላጫ ድምጽ መንግሥት መመሥረት የሚያስችለውን ውጤትም አግኝቷል።

ምርጫ ሕዝቡ በመሪዎች እና በፖሊሲዎች ላይ እንዲወስን የሚያስችል የዴሞክራሲ መገለጫ ነው። ከውጤቱ በኋላ የሕዝብ ድምፅ እንዲከበር ከተቋማት ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና እጅግ ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ከምርጫ ማግስት የሕዝብን ውሳኔ በጸጋ መቀበል እና በሕጋዊ ማዕቀፍ መንቀሳቀስ የሀገርን ሰላም ያሰፍናል።

በእርግጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ረጅም ጊዜ እና ቀጣይነት ያለው ጥረትን የሚጠይቅ መኾኑን በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት መምህር አበራ ታደሰ ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝቡ ጋር የሚገናኙት በምርጫ ጊዜ ብቻ ሳይኾን ቋሚ መድረክ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። ይልቁንም የሕዝቡን ፍላጎት፣ ችግሮች እና ቅሬታዎች በቅርብ በማዳመጥ የራሳቸውን አማራጭ ሀሳቦች ማበልጸግ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

የሕዝብን ድምጽ መሰረት በማድረግም መንግሥት የተሻለ ሥራ እንዲሠራ ገንቢ ትችቶችን ማቅረብ እና ግፊት ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።

በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያገኘው አካል መንግሥት ሲመሠርት አናሳ ድምጽ ያገኘው ወገን መብቱ፣ ሀሳቡ እና የመናገር ነጻነቱ ሊከበርለት እንደሚገባ ገልጸዋል። የምርጫን ውጤት በሰላማዊ መንገድ መቀበል እና ሂደቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አካል መኾኑን መረዳትም ያስፈልጋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መስመር ሳይወጡ ጠንካራ እና የተሻለ አማራጭ ሀሳብ ይዞ በመቅረብ በትግሉ መቀጠል ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። እነዚህን እሴቶች በማሳደግ በሀገሪቱ የፖለቲካ ባሕል እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዞኑ በግንባታና ጥገና የ792 ትምህርት ቤቶች ደረጃ ተሻሽሏል።
Next articleየኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ።