በዞኑ በግንባታና ጥገና የ792 ትምህርት ቤቶች ደረጃ ተሻሽሏል።

6

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ በትምህርት ጥራት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እና የትምህርት ተቋማትን ደረጃ ለማሻሻል ሰፊ ርብርብ እያደረገ መኾኑን አስታውቋል።

የመምሪያው ምክትል ኀላፊ ተፈሩ መላኩ አብዛኛዎቹ የትምህርት ተቋማት የነበረባቸውን መጎሳቆል፣ የምቾት አለመኖር እና የክፍል እጥረት ችግሮችን ለመፍታት ማኅበረሰቡን፣ የቀድሞ ተማሪዎችን፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን እና የመንግሥትን አቅም በማስተባበር ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

በዓመቱ 911 ሚሊዮን 290 ሺህ 911 ብር በጀት በመያዝ 518 የመማሪያ ክፍሎችን የያዙ 148 አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን አስታውሰዋል። እስካሁን 320 የመማሪያ ክፍሎችን ያካተቱ የ78 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ማከናወን መቻሉን አስታውቀዋል። ይህም የዕቅዱን 61 ነጥብ 78 በመቶ ያሳካ እና 38 ሚሊዮን 575 ሺህ 890 ብር የወጣበት ነው።

በሌላ በኩል የነባር ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። 9ሺህ 593 ልዩ ልዩ ክፍሎችን የያዙ 714 ትምህርት ቤቶች ጥገና ተደርጎላቸዋል። ይህም የዕቅዱ 108 ነጥብ 2 በመቶ ነው፤ ለዚህም 204 ሚሊዮን 415 ሺህ 882 ብር ወጭ መደረጉን ነው ያስታወቁት። በአጠቃላይ በአዲስ ግንባታ እና በጥገና የ792 ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ተችሏል ነው ያሉት።

ምክትል መምሪያ ኀላፊው የትምህርት ጥራት የሚለካው በግብዓት፣ በሂደት እና በተማሪዎች ውጤት ጥምረት መኾኑን ጠቁመዋል። የግብዓት ችግሮችን ከመቅረፍ ጎን ለጎን በትምህርት ሂደቱ እና በተማሪዎች የዓመት ውጤት ላይ ተጨባጭ መሻሻል ለማምጣት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

#አሚኮ_ዜና #የትምህርት_መሠረተ_ልማት_ዕድሳት_ሥራ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላምን ማረጋገጥ እና የኑሮ ጫናን ማቅለል የአሸናፊው ፓርቲ ትኩረት መኾን አለበት።