
ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምርጫ ቅድመ ዝግጅት፣ የድምፅ መስጫ ዕለት እና ድኅረ ምርጫ ሰላማዊ መኾን ለተረጋጋ መንግሥት እና ለሀገር ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በድኅረ ምርጫ ሂደት ውስጥ ትገኛለች።
በዚህ ወቅት ላለፉት የምርጫ ዓመታት የነበሩ አላስፈላጊ የፖለቲካ ልምዶችን በመቀየር ድኅረ ምርጫውን ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ምን ዓይነት የፖለቲካ አካሄድ መከተል ይገባል?
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህሩ አበራ ታደሰ የተጠናቀቀው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች የተሻለ የዴሞክራሲ ልምምድ የታየበት መኾኑን ገልጸዋል። በርካታ ዜጎች የተሳተፉበት፤ በሰላማዊ መንገድ የተጠናቀቀ እና በድኅረ ምርጫ ውጤት በሚገለጽበት ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጤቱን በጸጋ የተቀበሉበት እና የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት የተስተዋለበት መኾኑንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ያሸነፈው ፓርቲ በምርጫው ሕጋዊ ሥልጣን እና ተቀባይነትን አግኝቷል ብለዋል። ስለኾነም ሕጋዊነቱን ያረጋገጠው ፓርቲ እና የሚመሠረተው መንግሥት ባለፉት ዓመታት የሕዝቡ መሠረታዊ ችግሮች ኾነው ለቀጠሉት የሰላም እጦት እና የኢኮኖሚ ጫናዎችን መፍትሔ ለመስጠት መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ውይይት እና ድርድርን በማስቀደም የተጀመረውን የሀገራዊ ምክክር በማጠናከር ሰላም፣ ደኅንነትን ማስከበር እና ዜግች በነጻነት ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል ቀዳሚ የፖለቲካው ማጠንጠኛ ማድረግ አለበት ነወ ያሉት። በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች መግባባት እና ስምምነት እንዲኖር የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል።
በምርጫ ሕጋዊ ሥልጣን ያገኘ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኀላፊነት እንዳለበትም አንስተዋል።
ከውይይት እና ድርድር ይልቅ ግጭትን የሚመርጡ አካላትን በማስታገስም በመላው ሀገሪቱ ሰላም እና ደኅንነት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ሰላምን በማስፈን ሂደት ከመንግሥት ባለፈ ከማኅበረሰቡም ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል። በስፋት ወጥቶ በምርጫ የተሳተፈው ሕዝብ በተሳሳተ መረጃ ሳይታለል ከመረጠው መንግሥት ጎን ኾኖ ሰላምን ማስፈን ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
የፓለቲካ ፓርቲዎች ለሰላም እና ልማት መረጋገጥ፤ ለፖለቲካ ምሕዳር መስፋት፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሳካት የሚኖራቸው ሚና ጉልህ ነው ብለዋል።
በምርጫ መወዳደር ብቻ ሳይኾን በድኅረ ምርጫ ሂደቶች ለሀገሪቱ በጎ አሻራቸውን ማሳረፍ እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል።
ዘጋቢ ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
