🕊️ “ኢትዮጵያን ነፍጥ ጎድቷታል፤ ምክክር ይታደጋታል”

13

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 🇪🇹 በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ቅራኔዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር አስተማማኝ መንገድ ነው።

ይህ ታሪካዊ መድረክ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት እና የጋራ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል።

በጅንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ምስክር ከተማ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ ውስብስብ ችግሮችን በመሠረታዊነት ለመፍታት ያለመ ትልቅ እርምጃ መኾኑን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ የሚስተዋሉ አለመግባባቶች፣ በየቦታው የሚነሱ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ የታሪክ ተቃርኖዎች እና የፖለቲካ ሽኩቻዎች በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉት በምክክር ብቻ መኾኑን የዓለም ተሞክሮ ያስረዳል ነው ያሉት።

ምክክሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የሃይማኖት አባቶች እና ልዩ ልዩ ሃይሎች የጋራ መድረክ እንዲኖራቸው በማድረግ ለዓመታት ተዘግተው ለቆዩ ቅሬታዎች ቁልፍ መፍትሔን ያመላክታል ብለዋል።

ለመነጋገር ደግሞ መዘጋጀት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለሀገር የሚያስብ ሁሉ ለምክክሩ ቁርጠኛ ሊኾን ይገባል፤ በተለይም የፖለቲካ ልሂቃን ትልቅ ታሪካዊ ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።

የኃይል አማራጮች የፖለቲካ ፍላጎት ማሥፈጸሚያ ተደርገው ሊወሰዱ እንደማይገባም አስረድተዋል። የቱንም ያህል በመንግሥት ላይ መጠራጠር ቢኖር እንኳን ለሀገር ሲባል ለመነጋገር መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ነው የመከሩት።

🤝 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ “ኢትዮጵያን ነፍጥ ጎድቷታል ምክክር ይታደጋታል” በማለት ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ህልውና የሚኖረውን ጠቀሜታ ገልጸዋል።

ነፍጥ በየተራ እልቂትን፣ የሥነ ልቦና እና የአካል ጉዳትን፣ የአዕምሮ ስብራትን፣ የታሪክ ተወቃሽነትን የሚያስከትል አውዳሚ እና ኋላቀር መንገድ መኾኑንም አመላክተዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ እንዳብራሩት ነፍጥ አንድ ጊዜ አሸናፊ ያደረገውን አካል ሌላ ጊዜ ተሸናፊ ያደርጋል። ምክክር ግን ሁሌም ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የጋራ መሣሪያ ስለመኾኑም ያብራራሉ።

ሀገራዊ ምክክር በብዙ ሀገሮች ተሞክሮ ውጤት ያስገኘ ስለመኾኑም ይጠቁማሉ። ለኢትዮጵያም የሚያዋጣው ቁጭ ብሎ መነጋገር፣ መደማመጥ፣ መምከር እና የጋራ ሀገርን ለመገንባት መግባባት ላይ መድረስ ወሳኝ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያንም ቁጭ ብለው የሚመክሩበት ጊዜው አሁን ነው። ይህ ታሪካዊ ኀላፊነት የተጣለበት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በርካታ ሂደቶችን አልፎ የመጨረሻውን የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ ከሐምሌ 08/2018 ዓ.ም ጀምሮ ቀጠሮ ይዟል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

#አሚኮ #ሀገራዊ_ምክክር #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምግብን በማበልፀግ የሥርዓተ ምግብ ችግሮችን ለማቃለል እየተሠራ ነው።
Next articleሰላምን ማረጋገጥ እና የኑሮ ጫናን ማቅለል የአሸናፊው ፓርቲ ትኩረት መኾን አለበት።