
ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ባለፉት አራት ዓመታት ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል ምግብ ማበልፀግ ላይ የተከናወኑ ሥራዎችን ገምግሟል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ባለሙያ መለሰ እንግዳየሁ ምግብ፣ መድኃኒት እና መሰል ጉዳዮች በሰው ልጅ ጤና ላይ ጉዳት የማያደርሱ ኾነው እንዲዘጋጁ እና እንዲደርሱ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ብለዋል።
ከአምራች ፋብሪካዎች ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው በሚደርስበት ሂደት ቁጥጥር ይደረጋል ነው ያሉት። አጠራጣሪ ነገሮች ሲታዩም ምርመራ ተደርጎ ችግር ከተገኘ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል።
የሰላም እጦቱን ተከትሎ ፈዋሽነት የሌላቸው መድኃኒቶች እና የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮችን ያላሟሉ ምግቦች በስፋት እንደሚገኙም ነው የጠቆሙት። ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በፍጥነት ደርሶ እርምጃ ለመውሰድ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩም በቁጥጥሩ ላይ ችግር እየፈጠረ መኾኑን ጠቁመዋል።
የግሎባል አልያንስ ፎር ኢምፕሩቭድ ኒውትሬሽን የካስኬድ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ የኔው አምሳል ከሥርዓተ ምግብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማቃለል የስንዴ እና የዘይት ምርቶችን በቫይታሚን እና በማዕድናት ማበልጸግ ዋና ዘዴ ኾኖ መገኘቱን ገልጸዋል። በዚህም ከተቋማት ጋር በመቀናጀት ምግቦችን በቫይታሚን እና በማዕድናት ማበልፀግ ላይ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ 90 በመቶ የሚኾኑት የስንዴ ዱቄት አምራቾች እና 100 በመቶ የሚኾኑት የምግብ ዘይት አምራቾች በአግባቡ ምግብ እያበለፀጉ መኾናቸውን አብራርተዋል። በቫይታሚን እና በማዕድናት የበለፀጉት ምግቦች የሕጻናትን ዕድገት የሚያስተካክሉ እና ሰዎችን ከበሽታ የሚከላከሉ አስፈላጊ ምግቦች ናቸው ብለዋል።
ውይይቱ ባለፉት አራት ዓመታት ምግብን በማበልፀግ ሂደት የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገም መካሄዱንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት የሥርዓተ ምግብ የተለያዩ ችግሮች ያሉበት ነው ብለዋል። ችግሮችን ለማስተካከል በክልሉ የሚመረቱ እና ከውጭ የሚገቡ ምግቦች የበለፀጉ እንዲኾኑ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ትርፍ አምራች ከመኾን ባሻገር አጠቃቀምን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል። የሰላም እጦቱ የበለፀገ ምግብ ለማኅበረሰቡ እንዲቀርብ በሚደረገው ቁጥጥር ላይ እንቅፋት ኾኖ መቆየቱንም አንስተዋል።
ከአቅርቦት እና አጠቃቀም ጋር የተያያዘው ችግር የሚፈታው ምግብን በማበልፀግ ነው ብለዋል። በፋብሪካዎች የበለፀጉ ምግቦች እንዲመረቱ እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።ማኅበረሰቡም የበለፀጉ ምርቶችን የመጠቀም ልምዱን እያሻሻለ ነው ብለዋል።
አቶ መልካሙ ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል ምግብን ማበልፀግ እና ለማኅበረሰቡ ማሠራጨት ሀገር አቀፍ አቅጣጫ በመኾኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
#አሚኮ_ዜና #ሥርዓተ_ምግብ_ማበልጸግ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
