
ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ክልላዊ የፈጠራ ሥራ ዐውደ ርዕይ እና የጥናት እና ምርምር ሲምፖዚየም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ መርሐ ግብሩ በትምህርት ዘርፍ የተሠሩ የፈጠራ ሥራዎችን፣ የጥናት እና ምርምሮችን፣ የተገኙ ውጤቶችን ለማስተዋወቅ እና ለማበረታታት የሚያስችል ነው ብለዋል። መርሐ ግብሩ 22 ዞኖችን ያካተተ እንደኾነም ጠቁመዋል።
25 የአሻጋሪ ዕቅድ ሳይንስ የፈጠራ እና የምርምር ሥራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል። ለዚህም ቢሮው ለፈጠራ ሥራዎች እና ለሳይንስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ክልሉን የወከሉ የፈጠራ ሥራዎች እንደነበሩም አንስተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኀበሪዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ ታሪክ እና ጽኑ ሕዝብ ያላት ሀገር እንደመኾኗ ተፈጥሮን ቀድማ ያሰላሰለች ናት ብለዋል። በየትኛውም ዓለም ከፍ ባሉ ቦታዎች ላይ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እየሠሩ እንደሚገኙም አንስተዋል። አሁንም ልጆች ሕዝባቸውን ከድኅነት ለማውጣት በፈጠራ ሥራ መበርታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ፈጠራ ከአካባቢያችን በሚታዩ ነገሮች ላይ በመነሳት የሚሠራ ነው፤ የፈጠራ ሥራ የሚሠሩ ልጆችንም ማበረታታት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በፈጠራ ሥራ እንዲሳተፉ ምቹ ኹኔታ መፍጠር እንደሚገባም ነው ያነሱት።
ተማሪዎችም በሚገጥሟቸው ፈተናዎች ሳይበገሩ በድል ተወጥተው ሥራቸውን ዳር ማድረስ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ይህ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
