“ሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭን በመደመር መንግሥት ዕይታ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ

4
ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀረር ከተማ የተጀመረው “ሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭ” በመደመር መንግሥት ዕይታ ጥራት እና ፍጥነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ኾኑን የሀረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገልጸዋል።
ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ በሀረር ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የ”ሀኪም ጋራ ኢኒሼቲቭን” ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በመስክ ምልከታው ላይም ርእሰ መሥተዳድሩ እንደገለጹት “በአው ሀኪም” ተራራ ላይ እየተሠራ የሚገኘው ኢኒሼቲቩ የአዲሲቷን ሀረር ዓለም አቀፍ ምልክት ከመኾን ባሻገር ለክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ጉልህ ፋይዳ ያበረክታል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ለቱሪዝም መዳረሻነት እና ለሕዝብ መዝናኛነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መኾኑን አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የፕሮጀክቱ እውን መኾን የጎብኝዎች ቆይታን በመጨመር ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አንፃርም ሚናው ከፍ ያለ መኾኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱም 1ሺህ 870 ደረጃዎች እንደሚኖሩት እና 2 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የመሠረተ ልማት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ ፕሮጀክቱ አካባቢያዊ ሀብቶችን በመጠቀም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ተራራው ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖረው በማድረግ ተገቢውን ጥበቃ እንደሚደረግለት አመላክተው ለዚህም ሕገወጥ ግንባታን በመከላከል ረገድ በቅንጅት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ተራራውን አረንጓዴ የማልበስ ሥራ ይሠራል ብለዋል።
ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ እና ጥራት ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመው ለዚህም የተጠናከረ ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ ነው የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ስኬታማ ሥራዎችን ሠርታለች” ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር)
Next articleየአሜሪካ ማዕቀብ ማንሳት እና የቴህራን ማስተባበያ