
ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ)በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ ወይና ማርያም አካባቢ ሲንቀሰቀስ የነበረውን ጽንፈኛ ቡድን መደምሰሱን የሀገር መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።
በ10ኛ እዝ ኮር ስር የሚገኘው ክፍለ ጦር በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች ተሰባስቦ ጥቃት ለመፈፀም ሲዘጋጅ የነበረውን ጽንፈኛ ቡደን መደምሰሱን በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሸናፊ ብርቄ ተናግረዋል።
ሠራዊቱ በማዕከላዊ ጎንደር ምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ ወይና ማርያም ተብሎ በሚጠራ ቦታ የጥፋት ተልዕኮ ለመፈፀም በደብቅ ሲዘጋጅ የነበረን ኃይል በተጠና ሁኔታ ወታደራዊ ስውርነትን በመጠቀም ባንዳውን ከነ አመራሩ ሙሉ በሙሉ ደምስሷል ነው ያሉት። በርካታ የቡድን እና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች መማረካቸውን አስታውቀዋል።
በነበረው ውጊያ ብሬን፣ ስናይፐር፣ ክላሽ፣ ቦምብ፣ የወገብ ትጥቅ፣ የክላሽ ካዝና፣ የስናይፐር ካዝና በመማረክ ክፍሉ ከፍተኛ የጀግንነት ገድል መፈጸሙን ገልጸዋል።
ራሱን የአፄዎቹ ክፍለ ጦር ብሎ በመሰየም የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ሕዝብ ግንኙነት እና ሻለቃ አዛዥ በሚል ሲንቀሳቀስ የነበረውን አማረ አሸናፊን ጨምሮ ዘጠኝ የጽንፈኛው መሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ከሀገር መከለካያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በርካቶች እጅ መስጠታቸውንም አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
