ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምርጫ ሂደት ሰላማዊ የድምጽ አሰጣጥን ከማካሄድ ባሻገር የምርጫ ውጤትን በጸጋ መቀበል ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ ሰላም መረጋገጥ ወሳኝ ነው።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፍልስፍና መምህር ዓለምነህ አጋየ በኢትዮጵያ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ቦርድን ሕግ እና መመሪያ ባከበረ መልኩ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት የታዩ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን በድኅረ ምርጫ ወቅት ማስቀጠል ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ መኾኑንም ተናግረዋል።

ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች፦

በድኅረ ምርጫ ወቅት ፓርቲዎች ከመወቃቀስ በመውጣት የምርጫ ውጤትን በጸጋ መቀበል።

የምርጫ ቦርድን ሕግና መመሪያ እና የሕዝብን ድምጽ ማክበር።

ግጭትን ከሚቀሰቅሱ ተግባራት በመራቅ ለሀገር ሰላምና ደኅንነት መቆም።

ቅሬታ ካለ ለምርጫ ቦርድ ማቅረብ፤ ካልተፈታም ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በመውሰድ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ መፍታት እንዳለባቸው የፖለቲካ ምሁሩ አሳስበዋል።

ለማኅበረሰቡ፦

ብሔር እና ሃይማኖት ከሚያንጸባርቁ የግጭት እሳቤዎች ሙሉ በሙሉ መራቅ።

የመረጡት ፓርቲ ቢያሸንፍም ቢሸነፍም ውጤቱን በጸጋ በመቀበል ለሀገር ሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው ገልጸዋል።


ላሸነፈው ፓርቲ፦

ሕገ መንግሥትን ለማፍረስ እና ሥልጣንን በኀይል ለመንጠቅ በሚሞክሩ ኀይሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ።

ታጣቂ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ማድረግ፤ የሰላምን አማራጭ በማይቀበሉ ደግሞ ሕግን በማስከበር ዘላቂ ሰላምን ማጽናት።

በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስርን መፍጠር እና ሕዝብ በመንግሥት ላይ ዕምነት እንዲኖረው የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን እንዳለበትም ነው የገለጹት።

የሀገር ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው በሰላማዊ ድምጽ አሰጣጥ ብቻ ሳይኾን፣ የምርጫ ውጤትንም በበሰለ የዴሞክራሲ ባሕል እና በጸጋ መቀበል ሲቻል መኾኑንም የፖለቲካ ምሁሩ ተናግረዋል።