“አረንጓዴ አሻራችን በተባበሩ ክንዶች እና በመደመር የከበረ እሳቤ የመሥራት ምስክር ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ

1
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጽሕፈት ቤት ሠራተኞቻቸው ጋር በመኾን በጫካ ፕሮጀክት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አካሂደዋል።
“የአረንጓዴ አሻራችን እንደሀገር የውበት ምንጭ እና የኢኮኖሚ ተደማሪ አቅም ይሆናል ብለን አቅደን የሠራነው በውጤት ፍሬ አፍርቶ እየታየ ያለ ተግባር ነው” ብለዋል በዚሁ መርሐ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልእክት።
ይህ በተግባር የተደገፈ ግዙፍ የአረንጓዴ ልማት ጉዞ፣ ከኢኮኖሚያዊ እና የአካባቢ ጥበቃ ፋይዳው አልፎ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ረገድ ለሀገራችን ትልቅ ክብር እና ተሰሚነት ማጎናጸፉንም አንስተዋል።
የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ በመሳብ ላይ የሚገኘው ይህ ስኬት የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP32) በኩራት ለማስተናገድ ለሚደረገው ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጠንካራ እና አስተማማኝ መሰረት ጥሏል ነው ያሉት።
ይህ ሁለንተናዊ እመርታ የመንግሥትን እና የዜጎችን ትጋት የሚያሳይ፣ መላው ኢትዮጵያውያንን እጅግ ሊያኮራ የሚገባ ታላቅ ሀገራዊ ድል ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
“አረንጓዴ አሻራችን በተባበሩ ክንዶች እና በመደመር የከበረ እሳቤ የመሥራት ምስክር ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደውን ግብ ለማሳካት በኅብረት እንትከል፣ እንንከባከብ ሲሉም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከሁሉም በላይ ሀገር አሸንፋለች !
Next articleበቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት የታዩ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን በድኅረ ምርጫ ወቅት ማስቀጠል ከሁሉም ይጠበቃል።