ከሁሉም በላይ ሀገር አሸንፋለች !

7
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰላም ጀምራ በሰላም ፈጽማለችና ሀገር አሸንፋለች፤ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን በምርጫ ብቻ አድርጋለችና ሀገር ድል አድርጋለች፤ የዴሞክራሲ ልምምዷን አጠናክራለችና ሀገር ከፍ ብላለች፤ አይቻልም በተባለበት ጊዜ ችላለችና ሀገር አሸንፋለች፤ ከጦርነት ይልቅ ምርጫን አስቀድማለችና ሀገር ድል አድርጋለች።
ሥልጣን ከምርጫ ውጭ እንደማይገኝ አሳይተዋልና ኢትዮጵያውያን አሸንፈዋል፤ ድል አድርገዋል፤ የሀገራቸውን ሰላም በጋራ ለመጠበቅ ቃል ኪዳን አሥረዋል፤ በድምጻቸውም አደራ ሰጥተዋል፤ ጦርነትን እና ግጭትን ተጠይፈዋል፤ ከምርጫ ውጭ ያለው የሥልጣን ሽግግር ዘመኑ እንዳለፈበት አሳይተዋል።
ኢትዮጵያውያን በካርዳቸው እልፍ ጉዳይ ተናግረዋል፤ የሚወዷትን ሀገራቸውን፤ ተስፋቸውን እና ነጋቸውን አደራ ሰጥተዋል፤ አደራ ደግሞ ክቡር ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በምርጫ ዛቻዎችን፣ ማስፈራሪያዎችን እና ስጋቶችን ድል ነስተዋል፤ ከሁሉም በላይ የሀገራቸውን ሰላም አስቀድመዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ በሰላም ተካሂዷል። ትናንት ደግሞ የምርጫው አጠቃላይ ውጤት ይፋ ኾኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ቦርዱ አካታችነትን ዋነኛ መርሕ በማድረግ መሥራቱን አንስተዋል፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለው ግንኙነት በምርጫ ወቅት የተገደበ አይደለም፤ ሁልጊዜም እና ቀጣይነት ያለው ነው እንጂ ብለዋል።
ምርጫው በተያዘለት ጊዜ አይጠናቀቅም የሚል ጥርጣሬ እንደነበር ያነሱት ሰብሳቢዋ ቦርዱ ተቋማዊ ገለልተኛነቱን በመጠበቅ፣ ሕግ እና መመሪያን ብቻ በመጠቀም፤ በፖለቲካዊ ጫና ባለመመራት ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት ነጻ ኾኖ ሥራውን ሠርቷል ነው ያሉት።
የምርጫው ሂደት ስኬታማነት የአንድ ተቋም ብቻ አይደለም፤ የሕዝቡ፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የአጋር ድርጅቶች እና የሌሎች አካላት የጋራ ውጤት ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተደከመው ድካም፤ የተለፋው ልፋት ለሀገር ነበር ብለዋል። በሰባተኛው ምርጫ አዲስ የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ልምምድ ሥር እየሰደደ መምጣቱን ተመልክተናል፤ ምርጫው የሕዝብን ሰላም እና እፎይታን የሚያረጋግጥ ነው፤ ለረጅም ጊዜ ከቆየው እና ልዩነትን በጸብ፤ በአንባጓሮ ከመፍታት የሚያላቅቀን ልምምድ መኾኑን በተግባር አረጋግጠናል ነው ያሉት።
የጸብ እና የአምባጓሮ ልምምድ በሙሉ ተሽሯል ማለት አይቻልም፤ ልቦናቸው በዚያ የሚታትር፣ የመንፈስ ቅኝታቸው ይሄን የሙጥኝ ብሎ የሚይዝ፣ እስትንፋሳቸው ነውጥ የኾነ አያሌዎች ቢኖሩም ይሄን ያህል ሕዝብ ለምርጫ መውጣቱ የሚያሳየን ከዚህ ባሕል መላቀቅ እንደምንፈልግ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ስለ ምርጫው ጠቀሜታ እኛ ከምንገልጸው በላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይሄን ታላቅ ቁም ነገር በሕሊናው አሰናስሎ ይዞታል፤ በልቦናው አትሞታል ነው ያሉት።
ምርጫው ፖለቲካዊ ሁነት ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያዊው ማኅበራዊ ሃብትነቱን እና ጥሪቱን በተግባር ያሳየበት ታላቅ አምድ ነው፤ ሕዝባችን ስለ ኢትዮጵታዊ ቀናዒነቱ እና ፍቅሩ ጩኸቱን ሳይኾን የምርጫ ካርድ ድምጹን፤ ስላቅ እና ሐኬትን ሳይኾን ትሁትነቱን፤ የትኛውንም የፖለቲካ ሃሳብ ቢያራምድ ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ፍቅሩን ከጎኑ ላለው ወገን አለመንፈጉን ያሳየበት የተዋበ መድረክ ነበር ነው የሚሉት።
ብሩህነት የተገለጠበት፤ የሕዝባችን ፍቅር እና መተሳሰር የታየበት ነው፤ ይሄን የላቀ ዕውቀት ላሳየን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ምስጋና ብቻ ሳይኾን እና ጥልቅ አክብሮቴን አቀርባለሁ ነው ያሉት።
እያንዳንዱ ድምጽ ከዜጎች የተሰጠ ታላቅ አደራ ብቻ ሳይኾን የሕዝብ አገልጋይነት ማረጋገጫ የክብር ማሕተም ነው፤ የሕዝብ ማሕተምን የተቀበሉ አካላት ደግሞ በርትተው መሥራት አለባቸው ብለዋል።
የምርጫ ትልቁ በረከት ለሀገር ዘላቂ እድገት እና መረጋጋት ነው፤ ለነውጥ ምርጫ አይካሄድም፤ ለሁከት ድምጽ አይሰጥም፤ ኢትዮጵያውን ድምጽ የሰጡበት መንገድ ትልቅ መደላድል ነው ይላሉ።
ከምርጫ ውጭ ሥልጣን ለመያዝ ናፍቆት ያላችሁ ወገኖች የዘመናችን ዴሞክራሲ አስተማህሮቱ ሰላም እና እድገት፣ ቋንቋው ደግሞ መምረጥ እና መመረጥ ብቻ በመኾኑ የፖለቲካ ቅኝታችሁን እና አካሄዳችሁን ከዚሁ ሥልጡን መስመር ጋር ማስተካከል ይበጃችኋል ነው ያሉት። በምርጫ ሂደት ውስጥ ለማለፍ የማትሹ ከኾነ የሕዝብ ስጋት ምንጭ፤ የእድገት ሳንካ እና የጥፋት ተዋናይ ከመኾን ባሻገር ለኢትዮጵያ የምታተርፉት አንዳች ነገር የለም ብለዋል።
ከአሁን በኋላ የሕዝብ ድምጽ ያልጎበኘው፤ የምርጫ ካርድ ያልዳሰሰው የፖለቲካ ሥልጣን መያዣ መንገድ ዝግ መኾኑን ምርጫው መሠረት ጥሏል ነው ያሉት። ሌላ አማራጭ የምታስቡ ሁሉ ሕዝቡ እና ዘመኑ አይፈቅድምና ፈጥኖ ትክክለኛውን መስመር መያዝ የተገባ ነው፤ ሕዝባችን አሁን በደረሰበት የፖለቲካ ንቃት ደረጃ ጎታች ሃሳብን፣ አመጽን የማይፈቅድበት፣ ግጭትን ያነወረበት እና የተጠየፈበት እንደኾነም ገልጸዋል።
ሥልጡን መንገዱን የማትጠቀሙ ከኾነ ግን ቢበዛ ልትኾኑ የምትችሉት የዘመናችን የፖለቲካ ድርሳን ሲጻፍ የግርጌ ማስታወሻ ብቻ ነው ይላሉ።
ሕዝቡ ይመራኛል የሚለውን መርጧል፤ የተመረጣችሁ ደግሞ አደራችሁን በአግባቡ ተወጡ ነው ያሉት።
በምርጫ ሰላም አሸንፏል፤ ሀገር አሸንፋለች፤ የዴሞክራሲ ተስፋ በርቷል፤ ግጭት እና ጦርነት ተጠልቷል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየደብረ ታቦር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሐምሌ ወር ሥራ ይጀምራል።
Next article“አረንጓዴ አሻራችን በተባበሩ ክንዶች እና በመደመር የከበረ እሳቤ የመሥራት ምስክር ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ