የደብረ ታቦር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሐምሌ ወር ሥራ ይጀምራል።

5
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እየተገነባ የሚገኘው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት መምሪያ አስታውቋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት መምሪያ ኀላፊ ዓባይ አለባቸው በከተማ አሥተዳደሩ ለመሶብ የአንድ ማዕከል በሚመጥን መልኩ እየተገነባ የሚገኘው ፕሮጄክት 98 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። ማዕከሉን በሰኔ ወር ከ20 እስከ 25 ባሉት ቀናት በማስመረቅ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ 13 ተቋማት እና 101 አገልግሎቶች ወደ አንድ ማዕከሉ እንደሚገቡ የተናገሩት መምሪያ ኀላፊው የዲጂታል ሥርዓቶችን የመዘርጋት፤ የሰው ሀብትን የማልማት፤ የሠራተኞችን መረጃ ወደ ማዕከሉ ቋት የማስገባት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዓላማ ነው ብለዋል። በከተማ አሥተዳደሩ የአገልግሎት አሠጣጥ ክፍተት ያለባቸው እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ የሚነሳባቸው አገልግሎቶች ወደ ማዕከሉ ይገባሉ ነው ያሉት።
ከተለዩት ተቋማት ውስጥ በባሕሪ፣ በእውቀት እና በክሕሎት ብቁ የኾኑ ባለሙያዎች ተለይተው ሥልጠና በመውሰድ ላይ ናቸው ብለዋል። ሥልጠናውን ሲያጠናቅቁ ወደሥራ እንደሚገቡም አመላክተዋል።
ማዕከሉ በቴክኖሎጅ እና በብቁ ባለሙያ አገልግሎት የሚሰጥበት በመኾኑ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታት የደንበኞችን የአገልግሎት እርካታ ከፍ እንዲያደርግ ታልሞ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ይህ ማዕከል እና የተለዩት አገልግሎቶች እንደ ጅምር የሚወሰዱ መኾናቸውን የጠቀሱት መምሪያ ኀላፊው በቀጣይ ግንባታዎችን በማስፋፋት ሁሉንም ተቋማት ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስገባት በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበሰሜን ሸዋ ዞን በሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።
Next articleከሁሉም በላይ ሀገር አሸንፋለች !