🕊የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሌሎች የምክክር ሂደቶች በምን ይለያል?

2

 

ባሕርዳር: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክሩን ለማስተባበር ሥራውን ሲጀምር በስትራቴጂያዊ ዕቅዱ ካስቀመጣቸው ምሰሶዎች አንዱ እና ዋነኛው አጀንዳ የማሠባሠብ፣ የመለየት እና የመቅረጽ ተግባር እንደነበር ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን እና ኀላፊነት መሠረት አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማሠባሠብ በሂደቱ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን በመለየት የምክክር ሂደቱን ሲያስተባብር ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሠባሠብ የምክክር ምዕራፍን በማጠናቀቅ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው እየተንደረደረ ይገኛል፡፡

ኮሚሽኑ በቅርቡ የሚያስተባብረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እስካሁን ከተደረገው የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት በምን እንደሚለይ ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ ኮሚሽኑ አጀንዳን በሰፋፊ ሕዝባዊ ውይይቶች ያሠባሠበበት የምክክር ሂደት የሚከተሉት ቁልፍ ባህሪያት ነበሩት፡፡

👉ባለድርሻ አካላት እንደ ሀገር ያልተግባባንባቸውን እጅግ መሠረታዊ የኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን በውይይት በማዳበር ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።

👉የብዙ ባለድርሻ አካላት ሕመሞች፣ ሥጋቶች፣ ምኞቶች እና ተስፋዎች በአጀንዳ መልክ ቀርበዋል።

👉በሂደቱ ኮሚሽኑ ለምክክሩ ሂደት የሚጠቅሙ እጅግ በርካታ ግብዓቶችን ሠብሥቧል።

👉በአንፃራዊነት የተሳታፊዎችን ምቾት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለተሳታፊዎች ቅርብ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ ቦታዎች የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደቱ ተከናውኗል።

👉በሕዝባዊ ውይይት አጀንዳን የመሠብሠብ ሥራ ብቻውን ሁለት ዓመታትን ፈጅቷል፡፡

በአጠቃላይ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደቱ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው መካሄድ እንደ ቅድመ ሁኔታ በማገልገል የራሱን ከፍተኛ ሚና መጫወቱ ቢታወቅም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን የማይተካ መኾኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በመኾኑም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው

👉የሀሳብ ነፃነትን እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማዕከል በማድረግ የባለድርሻ አካላት ወኪሎች በኮሚሽኑ ተቀርፀው በቀረቡ የአጀንዳ ሀሳቦች ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚመካከሩበት ጥንቃቄ የተሞላው የምክክር ሂደት ነው፡፡

👉በምክክር ሂደቱ መግባባት በተደረሰባቸው ሀሳቦች ላይ በመመርኮዝ ምክረ-ሀሳቦች እና የተለያዩ አማራጮች የሚዘጋጁበት ሂደትም ነው፡፡

👉መርሃ-ግብሩ በመዲናችን አዲስ አበባ ይከናወናል፡፡

👉መርሐ-ግብሩ በየቦታው በተደረጉ የአጀንዳ ማሠባሠብ የምክክር ምዕራፎች በተሠብሣቢዎች በተመረጡ ተወካዮች ይከናወናል፡፡

👉መርሐ-ግብሩ ከ4ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

#አሚኮ_ዜና #የምክክር_ኮሚሽን_ሥራዎች #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገራዊ ምክክር የግጭት እና የፖለቲካ ስብራት አዙሪትን ለመጠገን ትልቅ አጋጣሚ ነው” የፖለቲካ ሳይንስ መምህር