“ሀገራዊ ምክክር የግጭት እና የፖለቲካ ስብራት አዙሪትን ለመጠገን ትልቅ አጋጣሚ ነው” የፖለቲካ ሳይንስ መምህር

6

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የዝግጅት ምዕራፉን አጠናቅቆ ወደ ተግባራዊ ምዕራፍ መሸጋገሩ ለሀገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት እና ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

ኮሚሽኑ በሀገሪቱ በስፋት በሚታዩ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አካታች እና ግልጽ ውይይቶችን በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር አልሞ እየሠራ ይገኛል።

​በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አበራ ታደሰ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎቿ የዘለቁ የትጥቅ ግጭቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የሚስተዋሉባት ሀገር ናት ብለዋል። ይህ የምክክር መድረክ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉድለቶችን እና መሠረታዊ ችግሮችን በመለየት ግጭትን ወደ መፍትሔ በመቀየር ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

​የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በኃይል የተመሠረተ መኾኑን የገለጹት መምህሩ ይህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ያለውን የፖለቲካ ባሕል በመቀየር እና ልዩነቶችን በጠረንጴዛ ዙሪያ በመነጋገር የመፍታት ልምድን ያዳብራል ነው ያሉት። ይህ ደግሞ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላው ነው የተናገሩት።

መንግሥት የሕዝቡን እውነተኛ ጥያቄዎች ተረድቶ ምላሽ እንዲሰጥ ያስችላል ብለዋል። ይህም በሕዝቡ እና በመንግሥት መካከል መደማመጥን እና መተማመንን ይፈጥራል ነው ያሉት። በሀገሩቱ አካታችነት እንዲረጋገጥ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት።

የሀገሪቱን የውጭ ዲኘሎማሲ ምህዳርን ያጎለብታል ነው ያሉት። በለተይም ባለፉት ዓመታት የነበረውን የግጭት እና የፖለቲካ ስብራት አዙሪትን ለመጠገን ትልቅ አጋጣሚ መኾኑን ገልጸዋል።

የትጥቅ ትግል ግጭትን አቁሞ ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

የፖለቲካ ልዩነቶችን በኃይል ሳይኾን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ በመኾን ለሀገራዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥቶ መሳተፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው።
Next article🕊የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሌሎች የምክክር ሂደቶች በምን ይለያል?