
ሰቆጣ: ሰኔ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወልዴ ገልጸዋል።
ዋግ ኽምራን ከበረሃማነት ለማላቀቅ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዋነኛ መፍትሄ መኾኑን የገለጹት የመምሪያ ኀላፊው ለዚህም በ41 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እስከ አሁን ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
በ360 ተፋሰሶች በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ተቋማት እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ እየተዘጋጀ መኾኑንም አብራርተዋል።
አቶ አዲሱ በዚህም ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ተዘጋጅቷልም ነው ያሉት።
የተዘጋጁ የችግኝ ዓይነቶችም ለዝናብ አጠር አካባቢዎች ተስማሚ የኾኑ ሀገር በቀል ችግኞች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች እና የደን ችግኞች መኾናቸውንም አክለው ተናግረዋል።
በ47ቱም የችግኝ ጣቢያዎች ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ በሰዓቱ ቀሪ ችግኞችን ለማፍላት እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ኀላፊው ዋግ ኽምራን ከበረሃማነት እና ከድርቅ ለመታደግ ሁሉም ማኅበረሰብ የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ ሊዘጋጅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሰቆጣ ከተማ 02 ቀበሌ የሚገኘው የበለስ ችግኝ ጣቢያ ሠራተኛ አቶ መንግሥቱ ኃይሌ እና አቶ ተገኘ አበራ ባለፉት ዓመታት ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሀገር በቀል ችግኞችን እንዳቀረቡ ገልጸው በተያዘው ዓመትም በችግኝ ጣቢያው የደን፣ የአትክል እና ፍራፍሬ ችግኞችን እንዳዘጋጁ ጠቅሰዋል።
በዋግ ኽምራ ባለፈው ዓመት የነበረው የችግኝ የጽድቀት መጠኑ 66 በመቶ የነበረ ሲኾን በተያዘው ዓመት የጽድቀት መጠኑን ከ80 በመቶ በላይ ለማድረስ እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደር እየተሠራ መኾኑ ተመላክቷል።
#አሚኮ_ዜና #የአረንጓዴ_አሻራ_ሥራ #ዋግኽምራ_ብሔረሰብ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
